TIKVAH-MAGAZINE
199K subscribers
18.9K photos
292 videos
70 files
2.48K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

#ኢትዮጵያ

ያግኙን +251913134524
加入频道
#የዛሬ (መስከረም 3 / 2015 )

🙋‍♂ ዶ/ር ዊሊያም ሩቶ የጎረቤታችን ኬንያ #5ኛው_ፕረዚዳንት ሆነው ቃለ መሃላ ፈጽመዋል። ከአሁን በኃላም ሩቶ የኬንያ ፕሬዜዳንት እየተባሉ የሚጠሩም ይሆናል። ዛሬ በዓለ ሲመቱ ላይ የኢትዮጵያ ጠ/ሚ ዶ/ር ዐብይ አህመድን ጨምሮ የጅቡቲ፣ የሶማሊያ እና የሌሎችም ሀገራት መሪዎችና የተለያዩ ሀገራት መንግስታት እና የተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።

🇰🇪 ዛሬ ቃለ መሀላ የፈፀሙት የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሚያከናውኑትን ተግባር #እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል። ፕሬዜዳንት ሩቶ፤  ኬንያታ ሊረዱን እና ሊደግፉኝ ፍቃደኛ ስለሆኑ አመስግናለሁ ሲሉም ተናግረዋል።

🕝 የደሴ ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ምክር ቤት መስከረም 3/2015 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ሆቴሎች፣ መጠጥ ቤቶች እንዲሁም የንግድ ቤቶች አገልግሎታቸውን እስከ ምሽቱ ሁለት 2:30 ድረስ አገልግሎት እንዲሰጡ እንዲሁም የባጃጅ ትራንስፖርት እስከ ምሽቱ 2:00፤ ታክሲዎችና ሌሎች ተሺከርካሪዎች ደግሞ እስከ ምሽቱ 3:00  ድረስ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ወስኗል።

📜 ለኪራይ የሚዘጋጁ ቤቶችን ዋጋ ደረጃ ለመወሰን የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ በዚህ አመት ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ተናግረዋል። ለችግሩ እልባት ለመስጠት ተዘጋጅቶ ሚኒስትሮች ምክር ቤት የደረሰው ረቂቅ አዋጅ፥ የኪራይ ውል ጊዜን ከመወሰን ባለፈ ለኪራይ የሚዘጋጁ ቤቶች ሊያሟሏቸው የሚገቧቸውን መሰረተ ልማቶች በግልጽ ያስቀምጣል ብለዋል።

⚽️ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ሀገራችንን የወከሊት ፋሲል ከነማዎች የመጨረሻ ልምምዳቸውን ዛሬ የሰሩ ሲሆን በነገው ዕለት ወደ ታንዚያ እንደሚያቀኑ ይጠበቃል። ፋሲል ከነማ በመጪው አርብ በአዛም ኮምፕሌክስ ስታዲየም የመልስ ጨዋታውን ከቡርንዲው ቡሙማሩ ጋር ያካሂዳል።

#TikvahEthiopia

@tikvahethmagazine
#የዛሬ (መስከረም 4 / 2015 )

🏭 የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሲሚንቶ ከፋብሪካ የሚወጣበትን አዲስ የዋጋ ተመን ይፋ አደረገ። በዚህ መሰረትም ሲሚንቶ ከፋብሪካ የሚወጣበት አዲሱ የዋጋ ተመን ዝቅተኛው 510 ብር ሲሆን÷ ከፍተኛው ደግሞ 683 ብር ከ44 ሳንቲም እንዲሆን ተወስኗል፡፡

🕐 የወልድያ ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ምክር ቤት የሰዓት እላፊ ገደብ ላይ የማሻሻያ ውሳኔ አሳልፏል። በዚህም ከቀኑ 12:00 ሰዓት ጀምሮ የነበረው የተሽከርካሪ የሰዓት እላፊ ወደ ምሽቱ 1:00 ሰዓት ሲሻሻል ከምሽቱ 1:00 ሰዓት ጀምሮ የነበረው የሰዎች እንቅስቃሴ የሰዓት እላፊ ገደብ ወደ ምሽቱ 2:00 ሰዓት ድረስ ተራዝሟል። ሌሎች ክልከላዎች እንደቀጠሉ ናቸው ተብሏል።

🤝 ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ከሆኑት ሪታ ላራንጂንሃ ጋር ተወያይተዋል። በዚህ ወቀትም የኢትዮጵያ መንግሥት በአፍሪካ ኅብረት ለሚመራው የሰላም ሂደት ቁርጠኛ መሆኑን የገለጹ ሲሆን ዳይሬክተሯ በበኩላቸው፤ የአውሮፓ ህብረት በአፍሪካ ኅብረት የሚመራውን የሰላም ሂደት እንደሚደግፍ ተናግረዋል።

🌾 በኦሮሚያ ክልል የ2015 በጀት ዓመት 1 ሚሊየን ሄክታር መሬት በመስኖ ስንዴ ልማት በማልማት 38 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለማግኘት መታቀዱ ተገልጿል።

🔄 የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ አዲስ ኃላፊ ተሾሞለታል። የቢሮው ኃላፊ የነበሩት ዶክተር ቀነአ ያደታ ወደ መሬት ማኔጅመንት አስተዳደር ቢሮ  በሀላፊነት በመዛወራቸው የቢሮው የሠላም እሴት ዘርፍ ም/ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ተክተዋቸዋል።

#TikvahEthiopia

@tikvahethmagazine
#የዛሬ (መስከረም 5/2015)

🇺🇳 እንደ UN OCHA መረጃ በሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል ዳግም ባገረሸ ግጭት በአማራ ፣ አፋር፣ እና ትግራይ ክልሎች በ10 ሺዎች ተፈናቅለዋል፤ የሰብዓዊ እርዳታ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ መግባት አቁመዋል፤ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ወደ መቐለ በረራ ተቋርጧል። UN OCHA በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ድጋፍ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

👏 የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የአፋር ክልላዊ መንግሥት በሰመራ እና አጋቲና መጠለያ ጣቢያዎች ተይዘው የነበሩ ሰዎች ኮሚሽኑ ባቀረባቸው ምክረ ሃሳቦች መሰረት እንዲለቀቁና በፍላጎታቸው መሰረት ወደመጡባቸው አካባቢዎች እንዲመለሱ መደረጉን እውቅና ሰጣለሁ ብሏል። በዚህ ተግባር የተባበሩ አካላትንም አመስግኗል።

🇲🇼 በማላዊ የፕሬዚዳንት ቻክዌራ አስተዳደር ስድስት የሬዲዮ ጣቢያዎች እና ሶስት የቴሌቭዥን ጣቢያዎች አመታዊ የፍቃድ ክፍያ ባለመክፈላቸው ምክንያት ተዘግተዋል። በዓመቱ መጨረሻም ከ20 በላይ የራዲዮ ጣቢያዎች ሊዘጉ ይችላሉ ተብሎም ተሰግቷል። ውሳኔው የሀገሪቱ የሚዲያ ምኅዳርን በማጥበብ የመናገር ነጻነትን ይጋፋል የሚል ትችት ቀርቦበታል።

🏗 ሳፋሪኮም ኢትዮጲያ በ60 ሚሊዮን ዶላር ለሚገነባው ዘመናዊ የመረጃ ማዕከል 10 ሺህ ካ.ሜ የለማ መሬት ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በኪራይ ተረክቧል፡፡ የሚገነባው የመረጃ ማዕከል በዋናነት አገልግሎት የሚሰጠው ለሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ቢሆንም ለሌሎች ተቋማትም አገልግሎት መስጠት የሚችል መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

🇪🇹 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት (እስከ መስከረም 2017) በዋና አሰልጣኝነት እንዲቀጥሉ በዛሬው ዕለት ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ስምምነት ፈፅመዋል።

⚽️ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የሴካፋ ከ 17 ዓመት በታች ውድድር ከመስከረም 20/2015 ጀምሮ የሚካሄድ ሲሆን የምድብ ድልድሉ በዛሬው ዕለት ይፋ ሆኗል። አስር ሀገራት በሚሳታፉበት ከ 17ዓመት በታች ውድድር ኢትዮጵያ በምድብ አንድ ከታንዛኒያ ፣ ከኤርትራ ፣ ከሶማሊያ እና ከደቡብ ሱዳን ጋር ተደልድላለች።

#TIKVAHETHIOPIA

@tikvahethmagazine
#የዛሬ (መስከረም 6/2015)

❗️ "የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ተሸጋገረ " እየተባለ በአንዳንድ የማህበራዊ ገፆች ላይ የሚሰራጨው መረጃ ምንጩ የማይታወቅ በትምህርት ሚኒስቴር ሆነ በሀገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ያልተገለፀ ነው። ተማሪዎች እንዲሁም የተማሪ ወላጆች ጥንቃቄ ልታደርጉ ይገባል።

🚘 ገንዘብ ሚኒስቴር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኢንቨስትመንትንና አስመጪዎችን የሚያበረታታ እንዲሁም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ የታክስ ማሻሻያ ተግባራዊ መደረጉን አስታውቋል። ከውጭ የሚገቡ ሆነ ሀገር ውስጥ የሚመረቱ የኤሌክትሪክ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች፣ የቤት አውቶሞቢሎችና የእቃ መጫኛ ተሽከርካሪዎች ላይ ዝቅተኛ የጉምሩክ ታሪፍ የሚጣልባቸው ሲሆን ከተጨማሪ እሴት ታክስ፣ ከኤክሳይዝ ታክስና ከሱር ታክስ #ነፃ እንደሚደረጉ ታውቋል፡፡

✂️ የግል መገልገያ እቃዎች ወደሀገር የሚገቡበትን ሁኔታ የሚወስነው በስራ ላይ ያለው መመሪያ ለህገወጥ ንግድ በር የከፈተና የአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ተፅዕኖ የፈጠረ በመሆኑ በመመሪያ ቁጥር 923/14 ተተክትቷል ተብሏል። በዚህም ቀድሞ ይፈቀዱ የነበሩ እቃዎች በ84% ዝቅ እንዲሉ ተደርጓል።

🌾 ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ አሕመድ ዛሬ ጠዋት በኦሮሚያ ክልል የዱግዳ እና የቦራ ወረዳዎች የስንዴ ኩታ ገጠም እርሻ የጎበኙ ሲሆን "ስንዴን ለውጪ ሀገር ገበያ ለማቅረብ ወደያዝነው ግብ ቀርበናል" ሲሉም በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

🇺🇸 አሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛዋ አምባሳደር ማይክ ሀመር ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ፣ ከሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮች፣ ከአፍሪካ ህብረት እና ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር #ውጤታማ ውይይት አድርገዋል ብላለች። "ለኢትዮጵያ #አንድነት#ሉዓላዊነት እና #የግዛት_አንድነት ቁርጠኛ ነን " ስትል ገልጻለች።

⚽️ በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የቅድመ ማጣርያ እየተካፈለ የሚገኘው ፋሲል ከነማ በድምር ውጤት 3ለ1 ቡማሙሩን በመርታት ወደ ቀጣዩ ዙር አልፈዋል። ፋሲል ከነማ በቀጣዩ ዙር የማጣርያ ደርሶ መልስ ጨዋታ የቱኒዚያውን ሴፋክሲያን የሚገጥሙ ይሆናል።

#TIKVAHETHIOPIA

@tikvahethmagazine
#የዛሬ (መስከረም 7/2015)

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በዛሬው ዕለት መጠነ ሰፊ የደንበኞች የኔትወርክ ሙከራውን በቢሾፍቱ፣ ሞጆ እና ደብረ ብርሃን ከተሞች መጀመሩን አሳውቋል። ይህ የደንበኞች ሙከራ የሳፋሪኮምን ኔትወርክ እየሞከሩ ያሉትን ከተሞች ቁጥር #ስምንት የሚያደርሰው ሲሆን ባለፉት ሦስት ሳምንታት ድሬዳዋ፣ ሐረር፣ ሐረማያ፣ ባሕር ዳር እና አዳማ ላይ ሙከራው መጀመሩ ይታወቃል።

🇪🇹 35ኛውን የዓለም የቱሪዝም ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ “አዲስ እሳቤ ለቱሪዝም” በሚል መሪ ቃል ከመስከረም 13 እስከ 15 ቀን 2015 ዓ.ም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እንደሚከበር ተገልጿል። በመርሐግብሩ ላይ አዲስ የቱሪዝም ስትራቴጂ ይፋ እንደሚደረግም ተጠቁሟል።

📖 በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት የተዘጋጀው የ4ኛ ክፍል የሒሳብ መፅሀፍ በውስጥ #ገፅ_18 ላይ " የግዕዝ ቁጥሮች ምልክቶች #በቀጥታ ከግሪክ ቁጥሮች የተወሰዱ ናቸው" የሚል ሀሳብ ይዟል በመባሉ በርካታ ዜጎችን አስቆጥቷል። የአዲስ አበባ ከተማ ት/ት ቢሮ ይህ ይዘት "በመጽሐፉ ውስጥ የማይገኝና ሆነ ተብሎ የተሰራጨ የሀሰት መረጃ" ነው ብሎታል። ሆኖም መፅሀፉ ውስጥ ገብቷል የተባለው ሀሳብ የታየው በሶፍት ኮፒ በተሰራጨው የመፅሀፉ ቅጂ ላይ እንደሆነ ወላጆች ጠቁመዋል። ቢሮው በPDF ስለተሰራጨው መፅሀፍ ያለው ነገር/የሰጠው ማብራሪያ የለም።

🚌 የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከአዲስ አበባ ጎዳናዎች ያነሳቸውን ውሎና አዳራቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ 1897 ዜጎች ፍላጎታቸውን መሰረት በማድረግ ወደየመጡበት አካባቢ በዛሬው ዕለት መሸኘቱን ገልጿል።

🙏 የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ አባቶች የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ዛሬ የጎበኙ ሲሆን  ለኢትዮጵያና ለግድቡ ሰራተኞች በስፍራው ፀሎት በማድረግ ግድቡን ባርከዋል።

🇸🇩 በሱዳን የደረሰውን ከባድ ጎርፍ ተከትሎ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 134 የደረሰ ሲሆን በርካታ ቤቶች ደግሞ ወድመዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ብቻ በሱዳን 20 ሰዎች በጎርፍ ምክንያት ህይወታቸው አልፏል።

@tikvahethmagazine
#የዛሬ (መስከረም 9/2015)

🇪🇷 ኤርትራ ዕድሜያቸው ከ55 ዓመት በታች የሆኑ ተጠባባቂ የጦር ኃይሉ አባላት በአስቸኳይ ሪፖርት እንዲያደርጉ እንደተጠሩ በበርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ቢዘገብም የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል መሬት ላይ ያለው እውነታ ሆን ተብሎ እንዲዛባ እና እንዲጋነን ተደርጓል፤ የተወሰኑ የተጠባባቂ ኃይል አባላት የተጠሩ ቢሆንም ቁጥራቸው ግን በጣም ጥቂት መሆኑን ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

🇸🇴 የጎረቤት ሶማሊያ መንግስት በ " አልሸባብ " ላይ መጠነ ሰፊ ዘመቻ እያካሄደ ሲሆን በዚህ ዘመቻ በርካታ የቡድኑን ታጣቂዎች መግደል ጨምሮ ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን ነፃ አድርጓል። በሂራን ክልል በያሶማን መንደር አቅራቢያ በትናንትናው እለት ባካሄደው ዘመቻ 75 የአልሸባብ ታጣቂዎች መገደላቸው የተገለጸ ሲሆን በአጠቃላይ በዚሁ ክልል እስካሁን በተካሄደ የፀረ ሽብር ዘመቻ ኦፕሬሽን 200 የቡድኑ ታጣቂዎች መገደላቸውና 30 መንደሮች ከአልሸባብ ነፃ መደረጋቸውን የሀገሪቱ ጦር አሳውቋል።

📚 የትምህርት ሚኒስቴር በአብዛኛው የሀገሪቷ አካባቢዎች የ2015 ዓ.ም ትምህርት ዘመን በዛሬው እለት መጀመሩን አሳውቋል።

📩 የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) ን ከ30 ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ለመመለስ የተሰባሰቡ አደራጆች የፓርቲውን መጠሪያ ወደ " የኢትዮጵያ ሌበር ፓርቲ " በመቀየር ለምርጫ ቦርድ በድጋሚ ማመልከቻ ማስገባታቸውን ኢትዮጵያ ኢንይደር አስነብቧል።

💐 በአፋር ክልል በሎጊያ ከተማ መለስተኛ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ተገልብጦ በደረሰ የመኪና አደጋ የ5 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በ10 ሰዎች ቀለል እና ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል። በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ አርሲ ዞን አዳባ ወረዳ "አይሱዙ ቅጥቅጥ" የህዝብ ማመላለሻ መኪና ተገልብጦ በደረሰው በአደጋ የ6 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በ15 ሰዎች ላይ ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል።

⭕️ የአዲስ አበባ ከተማ የመዳሃኒት፣ የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን በ2014 በጀት አመት በ2 ሺህ 537 የጤና ተቋማት ላይ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት 699 የጤና ተቋማት በተለያዩ መለኪያዎች ከደረጃ በታች ሆነው መገኘታቸው ተገልጿል። በዚህም 108 የጤና ተቋማት ደግሞ ለተወሰነ ጊዜ ሙሉ በሙሉ እንዲሁም 34 የጤና ተቋማት ደግሞ የተወሰነ አገለግሎት እንዳይሰጡ ታግደዋል።

🏃‍♂ በመጪው ጥቅምት 5/2015 ዓ.ም ዋሽንግተን ዲሲ ላይ “አብሮነት መሻል ነው” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው ግራንድ አፍሪካን ራን በዲሲ በአርቲስት ሰለሞን ቦጋለ ከሚመራው ህብረት ለበጎ የበጎ አድራጎት ድርጅት ጋር በትብብር ለመስራት ስምምነት ፈፅሟል፡፡ በዚህ ዝግጅትም የክብር ዶክተር ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ ታላላቅ ኢትዮጵያዊያን የኦሎምፒክ አትሌቶች፣ ታዋቂ ሰዎች እና አምባሳደሮች ከሰፊው ኢትዮጵያዊ የዲያስፖራ ማህበረሰብ ጋር ተገናኝተው የሚያሳልፉበት መድረክ መሆኑ ተገልጿል።

#TIKVAHETHIOPIA🇪🇹

@tikvahethmagazine
#የዛሬ (መስከረም 10/2015)

📑 በኢትዮጵያ ጦርነት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንዲያጣራ በተመድ የተቋቋመው የሰብዓዊ መብቶች የባለሙያዎች ቡድን (ICHREE) 19ኝ ገፆች ያሉት የመጀመሪያ ግኝት ሪፖርት አውጥቷል። ሪፖርቱ በሰላማዊ ዜጎች ላይ መደፈር፣ ወሲባዊ ጥቃቶች፣ የዘፈቀደ ግድያ እና ረሃብ እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋላቸውን ይገልጻል።

ኢትዮጵያ ለመርማሪ ቡድኑ በቀጥተኛ መግለጫ ምላሽ ባስትሰጥም በጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዘነበ ከበደ ICHREE ያወጣው ሪፖርት አስቀድሞ የታቀደ እና ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው መሆኑን አንስተዋል።

🇺🇸 የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር በኢትዮጵያ ከነበራቸው የ10 ቀናት ቆይታ በኃላ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫቸውም የኤርትራ ሠራዊት የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ ለጦርነት መሰለፉ ያሳስበናል፤ እንቃወማለንም ሲሉ ገልጸዋል።

"የተፋላሚዎች ቁልፍ ልዩነት እርስ በርስ መተማመም አለመዳበር ነው።" በማለት በመግጫቸው ጠቅሰዋል። አምባሳደሩ ማዕቀብን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄም "ቀዳሚው ትኩረታችን ዲፕሎማሲ ነው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። "አሜሪካ የኢትዮጵያን አንድነት፣ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ታከብራለች" ሲሉም ነው የተደመጡት።

🌳 የ2015 ዓ.ም የኢሬቻ በዓል መስከረም 21 " ሆራ ፊንፊኔ " ፤ መስከረም 22 በቢሾፍቱ " ሆራ ሃርሰዴ " እንደሚከበር የኦሮሞ አባ ገዳዎች በዛሬው ዕለት አስታውቀዋል፡፡

💐 መነሻውን ከመካነ ሰላም በማድረግ ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ ያደረገ ሲኖትራክ ተሽከርካሪ በለጋምቦ ወረዳ ልዩ ቦታው " እህል ማፍሰሻው " ከተባለው ስፍራ ሲደርስ መንገድ ስቶ በመገልበጡ በደረሰ የትራፊክ አደጋ 5 ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ 15 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሷል።

በአዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ የ5 አመቷን ህጻን የደፈረው ወልደሚካኤል አሚጋ የተባለ ግለሰብ በፅኑ እስራት ተቀጥቷል። ተከሳሹ ድርጊቱን አልፈፀምኩም በማለት ክዶ ቢከራከርም በዐቃቤ ህግ በቀረበበት ክስ እና ማስረጃ መሰረት ፍርድ ቤቱ በ14 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል።

#TIKVAHETHIOPIA🇪🇹

@tikvahethmagazine
#የዛሬ (መስከረም 11/2015)

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በተመድ መርማሪዎች የወጣውን ሪፖርት " እርስ በእርሱ የሚጣረስ / ተምታታ እንዲሁም ተጨባጭነት ነው " ሲሉ ውድቅ አድርገውታል። አክለውም ሪፖርቱ፤ ፖለቲካዊ ግብ ይዞ የተዘጋጀ መሆኑንም በመግለፅ አዘጋጆቹም ለፖለቲካዊ ሽፋንና ኢትዮጵያን ለማዳከም ያዘጋጁት ነው ብለዋል።

📣 የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን " በተለያዩ ወንጀሎች ጠርጥሬ ስፈልገው የነበረው ዘመነ ካሴን በቁጥጥር ስር አውያለሁ " ሲል ዛሬ አሳውቋል። የአማራ ፖሊስ ዘመንን በባህር ዳር ቀበሌ 3 በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ተደብቆ በህብረተሰቡ ጥቆማ እንደያዘው ገልጿል። ምርመራው የሚካሄደውም #በክልሉ ፖሊስ መሆኑንም አሳውቋል።

💵 ምርጫ ቦርድ በደቡብ ክልል ለሚያካሄደው ሕዝበ ውሳኔ አምስት መቶ አርባ አንድ ሚልዮን ሁለት መቶ ሰባ ሺህ አንድ መቶ አራት ብር ከሰማንያ ሁለት ሳንቲም (የ541,270,104.82) ተገማች በጀት ለኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረቡን በዛሬው ዕለት አሳውቋል።

🛩 የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ6 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በቦይንግ ኩባንያ አማካኝነት ጌቭን ስካይ ቴክኖ ከተባለ የጣሊያን ኤሮስፔስ አምራች ኩባንያ ጋር በሽርክና ‹‹ኢትዮጵያን ስካይ ቴክኖሎጂስ›› የተሰኘ የአውሮፕላን አካል አምራች ኩባንያ ማቋቋሙን ገልጿል። የማምረቻ ተቋሙ ለቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን የውስጥ አካል መሸፈኛ የሚውል ዕቃ የሚያመርት ሲሆን እስካሁን ለ6 ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች የሚሆን ምርት አምርቶ ለቦይንግ ኩባንያ ልኳል።

🔻 ከቀድሞው ከማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ጋር በ2006ዓ.ም ውል በመፈረም በሶማሌ ብሔራዊ ክልል ኦጋዴን ቤዚን ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች የነዳጅ ፍለጋና ልማት ላይ ተሰማርቶ የነበረው የቻይናው ኩባንያ ፖሊጂሲኤል ከብዙ ማስጠንቀቂያ በኋላ ውሉ መቋረጡን የማዕድን ሚኒስትሩ ኢ/ር ታከለ ዑማ አስታውቀዋል።

#TIKVAHETHIOPIA🇪🇹

@tikvahethmagazine
#የዛሬ (መስከረም 12/2015)

💐 በባህርዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ዋና ክፍል ኀላፊ ኮማንደር ዋጋዉ ታረቀኝ ፀጥታ እያስከበሩ በነበረበት ከምሽቱ 6፡00 ሰዓት አካባቢ በአንድ ግለሰብ በተተኮሰ ጥይት ተመተው ህይወታቸው አልፏል። የከተማው የሰላምና ፀጥታ መምሪያ
ከተማዋ አሁን ላይ አስተማማኝ ሰላም እና መረጋጋት ላይ እንደምትገኝ ገልጿል።

💐 የአማሮ ልዩ ወረዳ አስተዳደር ትላንት " ዶርባዴ " በተባለ ቀበሌ በደፈጣ በተፈፀመ ጥቃት 5 አርሶ አደሮች መገደላቸው እና 3 አርሶ አደሮች እንደ ቆሰሉ ገልጿል። ልዩ ወረዳው ጥቃቱ የተፈፀመው በህ/ተ/ም/ቤት አሸባሪ ተብሎ በተፈረጀው ኦነግ-ሸኔ እና  ሸኔ ባደራጃቸዉ የጥፋት ቡድኖች ነው ብሏል።

‼️ በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ጃርዴጋ ጃርቴ ወረዳ የፀጥታ ችግር መኖሩንና ንፁሃን ሰዎች ላይ በታጣቂዎች ጥቃት መከፈቱን ነዋሪዎች እየገለፁ ይገኛሉ። እስካሁን ባለው ሁኔታ በቁጥር ያልተለዩ ሰዎች ህይወት መጥፋቱን የገለፁት ነዋሪዎች አካባቢው አሁንም ባለመረጋጋቱ ተጨማሪ ጥፋት ስለሚደርስ የመንግስት የፀጥታ ኃይል ወደ ስፍራው ገብቶ እንዲያረጋጋ ተማፅነዋል።

💐 ትናንት ምሽት 1 ሰዓት ከ 45 አካባቢ መነሻቸውን ከጂካዎ ዲልድይ አድርገው ወደ መተሀር በመጓዝ ላይ ባሉ ሰዎች ላይ ከደቡብ ሱዳን ማሉዋል ጋኦት በሚባል ቦታ ላይ ተኩስ ተከፍቶ አንድ ሰው ሲገደል ፤ 6 ሰዎች መቁሰላቸውን የጋምቤላ ክልል ኮሚኒኬሽን ፅ/ቤት አሳውቋል። ከተሳፋሪዎቹ መካከል 3 ሰዎች የደረሱበት አለመታወቁም ነው የተገለጸው።

🔺 የጥቁር ገበያ ግብይት በሚካሄድባቸው አንዳንድ የአዲስ አበባ አካባቢዎች በሳምንቱ አንድ የአሜሪካ ዶላር ከ90 እስከ 92 ብር ይሸጥ ነበር ያለው ካፒታል ጋዜጣ ይህ ከመደበኛው የምንዛሪ ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ከ70 እስከ 75 በመቶ ልዩነት እንደነበረው ካፒታል ዘግቧል። በተለይ መኪና አስመጪዎች 1 ዶላር እስከ 100 የኢትዮጵያ ብር እየገዙ መሆኑን ነው የጠቆመው። የጥቁር ገበያን የምንዛሪ ልውውጥ መቆጣጠር ብዙ ያልሰመረለት መንግስት የችግሩን ትክክለኛ ምክንያት ለማወቅ ጥናት እያደረገ መሆኑን የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ፍቃዱ ድጋፌ ለጋዜጣው በሰጡት ቃል ተናግረዋል።

#TIKVAHETHIOPIA

@tikvahethmagazine
#የዛሬ (መስከረም 14/2015)

‼️ የመተሐራ ቲክቫህ ቤተሰቦች በሚኖሩበት የመተሀራ አካባቢ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት እንደሚገባ በላኳቸው መልዕክቶች አስገንዝበዋል። እዛው " መተሐራ " አካባቢ ከአምስት ቀናቶች በፊት አንድ የቀበሌ ሊቀመንበር ተገድሎ ነበር ፤ ከዚህ ግድያ በኃላም የአካባቢው ነዋሪዎች የሆኑ ሰዎች መገደላቸውን የመተሐራ ቤተሰቦቻችን ገልፀዋል። ከሚፈፀሙ ግድያዎች በተጨማሪ ደግሞ ታጣቂዎች ሰዎችን በማገት ከፍተኛ ገንዘብ (እስከ 2 ሚሊዮን ብር) ድረስ የመጠየቅ እንቅስቃሴ እየተበራከተ በመሆኑ ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ ነውና ከመቼውም በላይ ልዩ ትኩረት ይፈጋል ሲሉ አስገዝበዋል። [ተጨማሪ ያንብቡ]

📣 የመንግስት ኮሚኒኬሽን ባወጣው መግለጫ " ከሰሞኑ አሸባሪው ሸኔ ሆሮጉድሩ ወለጋ በንጹሐንና ዜጎችና በአካባቢው ሚሊሻ አባላት ላይ ግድያ ፈጽሟል። " ብሏል። መንግስት በመግለጫው ቡድኑ በንጹሐን ላይ የወሰደው በሁለት ምክንያቶች ነው " የመጀመሪያው በትናንትናው ዕለት የተደመሰሱበትን ጃል ኡርጂ የተባለውን የአካባቢውን የሸኔ አዛዥና ጀሌዎቹን ደም ለመበቀል ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የመስቀልንና የኢሬቻን በዓላት ከወዲሁ ለማወክ ነው " ሲል አብራርቷል። መንግስት በመግለጫው ላይ ምን ያህል ንፁሃን እንደተገደሉ ያለው ነገር የለም።

🔴 በአዲስ አበባ ከተማ በልደታ ክ/ከተማ ወረዳ 08 ልዩ ቦታው " ቀጠና አንድ " ተብሎ በሚጠራው አካባቢየፌዴራል ፓሊስ በመምሰል የአንድን ግለሰብ ቤት ለመዝረፍ የሞከሩ ግለሰቦች ሙከራቸው በህብረተሰቡ እና በፀጥታ ኃይሎች ትብብር መክሸፉን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ። የፀጥታ ሀይሎች ቀድሞም በነበራቸው ጥርጥሬ ዘራፊዎቹን ሲከታተሏቸው እንደነበረ የተገለፀ ሲሆን ዘራፊዎች ከውጭ ባስቀመጧቸው ግብር አበሮቻቸው ቀድሞ አዘጋጅተውት በነበረው " ኮድ 3 ኦሮ " በሆነ ተሽከርካሪ ሊያመልጡ ችለዋል። በአካባቢው የደህንነት ካሜራ ስለነበረ ጉዳዩን ፖሊስ ይዞት ክትትል እያደረገበት ይገኛል ተብሏል።

⚪️ ለ13 አመታት በአልሸባብ ቁጥጥር ስር የነበረው በሂራን ክልል ቡልቡርዴ እና በለድዌይን ወረዳዎች መካከል ያለው ዋና መንገድ የሶማሌ ብሄራዊ ጦር በአካባቢው ነዋሪዎች እገዛ ነፃ ማድረጉን አሳውቋል። የፕሬዜዳንት ሀሰን ሼክ ሙሀሙድ አስተዳደር በአልሸባብ ይዞታዎች ላይ እያካሄደ ያለውን እጅግ መጠነ ሰፊ ዘመቻ አጠናክሮ መቀጠሉ የተገለፀ ሲሆን በተለይም በሂራን ክልል በርካታ ቦታዎችን ከአልሸባብ ነፃ ማድረግ ተችሏል።

🇪🇹 የኢትዮጵያ መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረውን ግጭት በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት በሚደረግ የሰላም ድርድር ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑን ምክትል ጠ/ሚ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገልጸዋል። በተጨማሪም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ስር በሚደረግ የሶስትዮሽ ድርድር ጉልህ ተፅዕኖ በማያደርስ እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት መርህን መሰረት በማድረግ ልዩነቶችን ለመፍታት አሁንም ፅኑ አቋም አላት ሲሉ ለጉባኤው ተናግረዋል።

🇪🇷 ከ17ዓመት በታች የሴካፋ ውድድር ከኢትዮጵያ ጋር በአንድ ምድብ የተደለደለችው ኤርትራ በውድድሩ እንደማትሳተፍ በደብዳቤ አሳውቃለች። በምድብ አንድ ከአዘጋጇ ሀገር ኢትዮጵያ ፣ ታንዛኒያ ፣ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን ጋር ተደልድላ የነበረችው ኤርትራ ለአወዳዳሪው አካል ውሳኔዋን ማሳወቋ ተረጋግጧል። የሴካፋ ከ 17ዓመት በታች ውድድር ከመስከረም 20 እስከ ጥቅምት 9/2015 በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በስምንት ሀገራት መካከል የሚደረግ ይሆናል።

#TikvahEthiopia

@tikvahethmagazine
TIKVAH-MAGAZINE
#PositivePeaceBuilding ሰማንያ የሚሆኑ ወጣቶች በ16 ቡድን ተከፋፍለው የስዕል ውድድር ለማድረግ ተዘጋጅተዋል። ተወዳዳሪዎቹ አሸናፊ ለመሆን አወንታዊ የሰላም ግንባታ፤ የአብሮነትና የግጭት አፈታት ሚናን በሥዕል አጉልቶ ማሳየትና ማስተዋወቅ ይጠበቅባቸዋል። ለውድድር የሚያበቃቸውን የሥዕል ሥራም የፊታችን ቅዳሜና እሁድ መስከረም 14 እና 15 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ አለ የሥነ ጥበብ…
#የዛሬ (መስከረም 15/2014)

🗓 የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓትን (e-GP) ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጾ ከዚህ በፊት በባለስልጣን መ/ቤቱ ድረ-ገጽ ላይ የተመዘገቡ አቅራቢዎች ምዝገባቸው ተቀባይነት የሚኖረው የኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓትን (e-GP) መጠቀም ባልጀመሩ ተቋማት ብቻ እስከ ህዳር 30 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ መሆኑን አስገንዝቧል።

📰 ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው ተልዕኮ ውጪ ለሆነ #የፖለቲካ_ሥራ እንደሚውል በፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ያጠናውን ጥናት ዋቢ አድርጎ ሪፖርተር ጋዜጣ ዘገባ ሰርቶ ነበር። ኮሚሽኑ በበኩሉ ዘገባው ኮሚሽኑ በቅርቡ በትምህርት ዘርፍ ካስጠናው ጥናት ጋር የማይጣጣም ነው ሲል ቢያስተባብልም አድርጌዋለሁ ያለውን ጥናት (ትክክለኛውን ማለት ነው) በይፋ አላሰራጨውም።

🔥 በመስቀል አደባባይ የሚካሄደው የደመራ ፕሮግራምን መጠናቀቅ ተከትሎ በከተማው በተለያዩ ደብሮች እና መንደሮች ደመራ የማብራት ስነ-ስርዓት ይካሄዳል። ይህን ተከትሎ በየአካባቢው ደመራ ሲበራ ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደረግ እና በማንኛውም ሁኔታ ርችት መተኮስ ፍፁም ክልክል መሆኑ ተልጿል።

🇪🇹 ሀገራችን የምታስተናግደው የሴካፋ ከ 17ዓመት በታች ውድድርን ለመካፋል ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ጀምረዋል። በዛሬው ዕለትም የዩጋንዳ እና ጅቡቲ ብሔራዊ ቡድኖች አዲስ አበባ መግባታቸው ለማወቅ ተችሏል። በውድድሩ የሚሳተፉ #ስምንት ሀገራት ከነገ ጀምሮ የ "MRI" ምርመራን የሚያካሂዱ ይሆናል።

⚽️ የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ የአስራ ስድስተኛው የአዲስ አበባ ዋንጫ አሸናፊ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። መቻልን የገጠሙት ፈረሰኞቹ በሀብቶም ገብረ እግዚአብሔር ብቸኛ ግብ 1ለ0 አሸንፈዋል።

#Update: በታዳጊና ወጣት ሰዓሊያን መካከል አወንታዊ ሰላም ላይ ያተኮረ የስዕል ውድድር https://yangx.top/tikvahethiopia/73901?single

@tikvahethmagazine
#የዛሬ (መስከረም 17/2015)

‼️ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)
በኦሮሚያ ክልል፣ ሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን ሲቪል ሰዎችን ኢላማ ያደረጉ ጥቃቶች አሁንም ተሰፋፍተው መቀጠላቸው ገልጾ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን አስገንዝቧል። በዞኑ በአሙሩ፣ በሆሮ ቡልቅ እና በጃርደጋ ጃርቴ ወረዳዎች ከነሐሴ 25 ጀምሮ ባሉት 3 ሳምንታት ውስጥ ብቻ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ ኦነግ ሽኔ)፣ በአማራ ኢመደበኛ ታጣቂ ኃይሎች እና ግለሰቦች በተከታታይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ከ100 በላይ ሲቪል ሰዎች የተገደሉ መሆኑ ታወቋል ገልጿል።

💐 ተወዳጁ ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ዛሬ ረፋድ 3፡00 ሰዓት አካባቢ ህይወቱ አልፏል። አርቲስቱ ዛሬ ጠዋት ላይ ሕመም ተሰምቶት ወደ አንድ የሕክምና ማዕከል አቅንቶ ሕክምና ያደረገ ሲሆን ከቆይታ በኋላ ህይወቱ እንዳለፈ ነው የተነገረው። የድምጻዊ ማዲንጎ አስክሬን ሕይወቱ ካለፈበት የግል ክሊኒክ ወደ አቤት ሆስፒታል ተወስዷል። ፖሊስ የድምጻዊውን ሞት መንስኤ ለማወቅ የአስክሬን ምርመራ ውጤቱን እየተጠባበቀ መሆኑን ገልጿል።

ከሐምሌ 18/ 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተቋርጦ የቆየው ቪዛቸዉ እና የመኖሪያ ፈቃዳቸው የሚፀናበት ጊዜ ከአንድ ወር በላይ ላለፈባቸው ግለሰቦች የቪዛ ማራዘምና የመኖሪያ ፈቃድ እድሳት ከመስከረም 16 2015 ዓ.ም. ጀምሮ አገልግሎቱን መስጠት መጀመሩን የኢፌዲሪ የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አስታውቋል።

💡 በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳ ከተማ በታወር ብረት ስርቆት ምክንያት ለአራት ቀናት ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል በተደረገው ጊዚያዊ ጥገና ከመስከረም 16 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ኃይል አንድታገኝ መደረጉ ተገልጿል።

🇪🇹 የኢትዮጵያ ከ 23ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለሞሮኮው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ባደረገው የቅድመ ማጣርያ ውድድር ድል ሳይቀናው ቀርቷል። ከዲሞክራቲክ ኮንጎ ጋር ጨዋታውን ያደረገው የ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኑ ከሜዳው ውጪ 1ለ0 ተሸንፏል።

#TikvahEthiopia

@tikvahethmagazine
#የዛሬ (መስከረም 18/2015)

📎 ኢሰመኮ በጋምቤላ ክልል፣ ጋምቤላ ከተማከሰኔ 7 እስከ 9 ቀን 2014 በክልሉ የጸጥታ ኃይሎች፣ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ ኦነግ ሸኔ) በጋምቤላ ነጻነት ግንባር መካከል የተደረገውን ውጊያ ተከትሎ ያካሄደውን የምርመራ ሪፖርት ይፋ አድርጓል። በዋናነት በክልሉ የጸጥታ ኃይሎች በተወሰዱ እርምጃዎች ሴቶችና የአዕምሮ ሕመምተኞችን ጨምሮ ቢያንስ 50 ሲቪል ሰዎች በተናጠል እና በጅምላ ከፍርድ ውጪ መገደላቸውን የጠቀሰው ሪፖርቱ የኦነግ ሸኔ እና ጋነግ ታጣቂዎችም በተኩስ ልውውጡ ወቅት “ተኩሳችሁብናል” በሚል ምክንያት እና በመንገድ ላይ ሲንቀሳቀሱ ያገኟቸውን ቢያንስ 7 ሲቪል ሰዎችን ገድለዋል ብሏል።

🚘 የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ ያተኮረ ታዳሽ ኃይል የ‹‹ትራንስፖርት ትምህርት›› በድኅረ ምረቃ ደረጃ ከዚህ ዓመት ጀምሮ ሊሰጥ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ትምህርትን በማስተርስ ደረጃ ለመስጠት የካሪኩለም ቀረፃ እና ግምገማ መጠናቀቁን የዩኒቨርሲቲው ኤሌክትሪካልና ኮምፒዩተር ኢንጂነሪንግ ፋኩልቲ ዲን ረ/ፕ/ር ቴዎድሮስ ጌራ ገልጸዋል፡፡

📈 ከመስከረም 18 ቀን 2015 ዓ.ም እኩለ ሌሊት 6:00 ሰዓት ጀምሮ የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ማስተካከያ የተደረገ ሲሆን በዚህም ቤንዚን በሊትር 57 ብር ከ05 ሳንቲም፣  ነጭ ናፍጣ በሊትር 59 ብር ከ90 ሳንቲም፣ ኬሮሲን በሊትር 59 ብር ከ90 ሳንቲም መሆኑ ተገልጿል፡፡ የሕዝብ ትራንስፖርት ተሽክርካሪዎች በሚጠቀሙት ነዳጅ ላይ በ2ኛው ምዕራፍ ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ አልተደገረም።

🚫 መነሻዋን ከናይሮቢ ኬንያ መዳረሻዋን አዲስ አበባ ያደረገች ግለሰብ 97 ኪሎግራም የሚመዝን እና ከ773 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያለው ኮኬይን የተባለ አደንዛዥ ይዛ ለመግባት ስትሞክር በአዲስ አበባ ኤርፖርት በቁጥጥር ስር ውላለች።

📴 ኢትዮ ቴሌኮም በአንደኛው ዋና ጣቢያው (core site) ላይ ባጋጠመው የውስጥ የኃይል አቅርቦት ቴክኒካል ችግር ምክንያት ዛሬ ከሰዓት በከፊል ደንበኞቹ ላይ የአገልግሎት መቆራረጥ ችግር አጋጥሞት እንደነበር ገልጿል። ለተፈጠረው ችግር ይቅርታ የጠየቀው ኢትዮ ቴሌኮም ችግሩ የተፈታ መሆኑን አሳውቋል።

🇸🇴 የሶማሊያ ኘሬዝደንት ሃሰን ሼክ መሃሙድ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ አዲስ አበባ ገብተዋል። ፕሬዚደንት ሃሰን ሼክ መሃሙድ ቦሌ አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የኢፌዴሪ ጠ/ሚ ዶ/ር ዐብይ አህመድ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ስራ ሃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

💐 የተወዳጁ ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ የቀብር ሥነ ስርዓት ነገ መስከረም 19 ቀን 2015 ዓ/ም ይፈጸማል። ከቀብር ሥነ ስርዓቱ አስቀድሞም ነገ በድምፃዊ ማዲንጎ መኖሪያ ቤት እንዲሁም በወዳጅነት ፓርክ ከ6 ሰዓት ጀምሮ ስንብት የሚካሄድ ሲሆን ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ በመንበረ ጸባኦት ቅድስተ ሥላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ሥርዓተ ቀብሩ እንደሚፈጸምም ተገልጿል።

💐 በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን አደዓ በርጋ ወረዳ ዛሬ ከቀኑ 6፡30 ላይ ከኢንጪኒ ከተማ ወደ ሽኖ ከተማ ሰዎችን አሳፍሮ ሲጓዝ በነበረበት ወቅት ከከባድ መኪና ጋር ተጋጭቶ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ15 ሰዎች ህይወት አልፏል።

#TikvahEthiopia

@tikvahethmagazine
#የዛሬ (መስከረም 20/2015)

🚫 መነሻቸዉን ከአማራ ክልል አድርገዉ ወደ አዲስ አበባ የሚሄዱ መንገደኞች በኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ኀይሎች ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ በመከልከላቸዉን እንግልት እየደረሰባቸው መሆን ጠቁመዋል። የኢሬቻ በዓል እስኪያልፍ ድረስ አዲስ አበባ መግባት አትችሉም መባላቸዉን አሚኮ ያነጋገራቸው ተመላሾች ጠቅሰዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልል የሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ቢሮ ምክትል ኀላፊ የሆኑ ኮሎኔል አበበ ገረሱ ለቀረበላቸው ጥያቄ "ይህንን ጉዳይ አላዉቀዉም ችግሮች ካሉም እናስተካክላለን " ብለዋል፡፡

🇺🇸 አሜሪካ ፤ " ኤርትራ በኢትዮጵያ ፤ ትግራይ ክልል ዳግም ግጭት እንዲቀሰቀስ በማድረግ ዋነኛውን ሚና በመጫወት ላይ ናት " ስትል ገልፃ ኤርትራ በአስቸኳይ ወደ ድንበሯ እንድትወጣ ጠይቃለች። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ አሜሪካ ፤ ኤርትራ ወደ ድንበሯ እንድትወጣ መጠየቋን ገልፀዋል። ወደ ሰላም እና ደህንነት የሚመለሰው ብቸኛው መንገድ አሜሪካ የምትደግፈው በአፍሪካ ኅብረት (AU) የሚመራው የሰላም ሂደት ነው ሲሉም ነው የተደመጡት።

🇸🇴 የሶማሊያ ፕሬዜዳት ሀሰን ሼክ ሙሃሙድ የሁለት ቀን ይፋዊ የስራ ጉብኝት አድርገው ዛሬ ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል። የሁለት ቀን የስራ ጉብኝቱን ተከትሎ የሁለቱም ሀገራት መሪዎች የተስማሙባቸው ነጥቦችን የያዘ መግለጫ ለህዝብ ተሰራጭቷል። ከዚህም ውስጥ ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት በጋራ የሚያደርጉትን ጥረት እና ሽብርተኝነትን በብቃት ለመዋጋት የሚሰራውን ስራ ሊያበላሽ የሚችሉ ተገቢ ያልሆነ የውጭ ጣልቃ ገብነቶችን ተፅእኖ መቀነስ ላይ ተስማምተዋል ተብሏል።

የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በሚሰጥበት ወቅት በዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ተማሪዎች ተቋማቱን ለቀው እንዲወጡ የትምህርት ሚኒስቴር አቅጣጫ ማስቀመጡ ይታወሳል። ጦርነትና የፀጥታ ችግር ካለባቸው የትግራይ፣ አማራ እና ኦሮሚያ አካባቢዎች የመጡ ተማሪዎችን በተመለከተ እስካሁን ምላሽ አልተሰጠም። የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ህብረት ፈተናው እስከሚጠናቀቅ ተማሪዎቹ የሚቀመጡበት ቦታ እንዲመቻችላቸው ትምህርት ሚኒስቴርን መጠየቁን ለቲክቫህ ገልጿል።

⚽️ የ2015ዓ.ም የቤት ኪንግ ኢትዮጲያ ፕሪሚየር ሊግ ከዛሬ ጀምሮ መካሄዱን ሲጀምር ውድድሩ የመጀመሪያውን አንድ ወር በባህዳር አለም አቀፍ ስታዲየም ይካሄዳል። አርባምንጭ ከተማን የገጠሙት ወልቂጤ ከተማዎች በአምበላቸው ጌታነህ ከበደ ብቸኛ ግብ ሶስት ነጥብ አግኝተዋል። በሌላኛው ጨዋታ በአዲስ አሰልጣኝ ደግያረጋል ይግዛው እየተመሩ የውድድር ዓመቱን የጀመሩት ባህር ዳር ከተማዎች ከመመራት ተነስተው አዲስ አዳጊውን ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2ለ1 ረተዋል።

#TikvahEthiopia

@tikvahethmagazine
#የዛሬ (መስከረም 21/2015)

🌳 የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል በአዲስ አበባ ከተማ ዛሬ በድምቀት ተከብሮ ውሏል። አስተዳደሩ በዓሉ ባህላዊ እሴቱንና ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ #በሰላም ተከብሮ መጠናቀቁን ነው ያስታወቀው።

የግሸን ማርያም ዓመታዊ ንግስ በዓል በድምቀት #በሰላም ተከብሯል። በዘንድሮው በዓል 1.5 ሚሊዮን የሚደርስ ሰው መታደሙን የአምባሰል ወረዳ ባህል እና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት አሳውቋል።

📣 ዛሬ ከመተሐራ ቤተሰቦች የመጣው መልዕክት ፤ ትላንት ከጠዋቱ መተሐራ አባድር 2ተኛ ካምፕ በሚባል አካባቢ ታጣቂዎች ገብተው #ከ10 በላይ ሰዎችን መገደላቸውን ፤ በዚህም ጥቃት ሳቢያ ደህንነታቸው አደጋ ላይ የወደቀባቸው ሰዎች መኖሪያቸውን ለቀው እንዲወጡ መገደዳቸውን ያመለክታል። የሟቾች ስርዓተ ቀብርም ዛሬ ተፈፅሟል ብለዋል። ከቀናት በፊት በአከባቢው በአጠቃላይ የደህንነት ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ስለመድረሱ በዝርዝር አመልክተው ነበር።

🔴 አማሮ ልዩ ወረዳ ጎልቤ ቀበሌ ልዩ ስሙ "መንደር" በተባለ ቦታ በመስከረም 19/2015 ዓ/ም በአንድ ቤተሰብ አባላት ውስጥ በ6 ሰዎች ላይ አጣዳፊ ተቅማጥና ትኩሳት በሽታ ምልክት መታየቱና ከዚህ ቤተሰብ አባላት ውስጥ አንድ ሰው ወደ ህክምና ማዕከል ሳይወሰድ በመቅረቱ ህይወቱ ማለፉ ተገልጿል። የበሽታው ምንነት #በላብራቶሪ እየተጣራ መሆኑ ተጠቅሷል።

🔺 በጋምቤላ ክልል ከ17 ወራት በኋላ #የጊኒዎርም በሽታ በአንድ ሰው ላይ መገኘቱን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ። በሽታው በአቦቦ ወረዳ በእርሻ ኢንቨስትመንት በቀን ሰራተኝነት ስራ  በተሰማራ ግለሰብ ላይ እና  በጎግ በአቦቦ ወረዳ በ3 እንስሳት ላይ መገኘቱን ነው የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ታች ኮንግ ገልጸዋል።

የወልድያ ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ም/ቤት ነባራዊ ሁኔታን ታሳቢ በማድረግ ተጨማሪ ክልክለዎችን አስተላልፏል። በዚህም ከነገ መስከረም 22  ቀን ጀምሮ #ጫት ወደ ከተማዋ ማስገባት፣ ጫት መቃም ሆነ ማስቃም በጥብቅ ተከልክሏል። በተጨማሪም የጎዳና ላይ ቁማር (ቢንጎ የመሳሰሉትን) መጫወት ተከልክሏል።

💬 ትላንት አርብ ወደ አዲስ አበባ ከተማ መግባት ሳይችሉ ቀርተው መንገድ ላይ እየተጉላሉ ከነበሩ መገደኞች መካከል የሆኑ የቲክቫህ ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት ዛሬ መንገዱ ተከፍቶ #በሰላም አዲስ አበባ መግባታቸውን በፅሁፍ መልዕክት አሳውቀዋል።

📢 የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ማስተካከያ ተግባራዊ ማድረጉ ይታወቃል። ከዚህ ጋር በተያያዘ፤ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ የሆኑ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች በሚጠቀሙት ነዳጅ ላይ ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ #ያልተደረገ በመሆኑ ህብረተሰቡ ይህን አውቆ መንግስት ካስቀመጠው ታሪፍ ውጪ ባለመክፈል ተባባሪ እንዲሆን ጠይቋል።

🇪🇹 በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአልጄርያው የቻን አፍሪካ ዋንጫ ተጋጣሚውን አውቋል። በአልጀርስ በተካሄደው የእጣ ማውጣት ስነ-ስርዓት ዋልያዎቹ በምድብ አንድ ከአዘጋጇ ሀገር አልጄርያ ፣ ሞዛምቢክ እና ሊቢያ ጋር ተደልድላለች።

⚽️ የአምናው የሊጉ ሻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ አዲስ አዳጊው ኢትዮጵያ መድህንን በሰፊ የግብ ልዩነት 7 ለ 1 በመርታት አመቱን በድል ጀምረዋል። ድሬዳዋ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ያደረጉት ጨዋታ ሁለት አቻ ተለያይተዋል።

#TikvahEthiopia

@tikvahethmagazine
#የዛሬ (መስከረም 22/2015)

🌳 የ2015 የሆራ ሀርሰዴ በዓል በቢሾፍቱ ዛሬ በድምቀት ተከብሯል። በዓሉ በሰላም ተከብሮ መጠናቀቁንም የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን አሳውቋል።

የጋምቤላ ክልል መንግስት የኢሰመኮን ሪፖርት "ለጠላት የወገነ ነው" ሲል ገልጾ ሪፖርቱን እንደማይቀበለውና እንደሚያወግዘው አስታውቋል። ሪፖርቱ "ከሁሉ በላይ በክልልና በአገር ላይ ይደርስ የነበረ ከፍተኛ ጥቃት በመቀልበስ ሂደት የህይወት መስዋዕትነት የከፈለውን የፀጥታ ተቋማችንን በጅምላ የፈረጀና የተገኘውንም ድል በዜሮ ያባዛ ሆኖ አግኝቶታል" ሲል ነው ክልሉ የገለጸው።

👨‍💻 የትምህርት ሚኒስቴር በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የኦንላይን ትምህርት ለመስጠት የዕውቅና ፍቃድ ጥያቄን ጨምሮ የተለያዩ ዝግጅቶች ማድረጉን ገልጿል። ሚኒስቴሩ ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመነጋገር ኢ-ለርኒንግን ለማስፋፋት ፕሮጀክት ቀርጾ የ22 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማግኘቱንና በአሜሪካው አሪዞና ዩኒቨርሲቲ አማካይነት መርሃ ግብሩን ዕውን ለማድረግ ሥራዎች መጀመራቸው ነው የተገለጸው፡፡

💐 የፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም ፋውንዴሽን  ዓመታዊ ኮንፈረንስ እና የፕሮፌሰር መስፍን እረፍት 2ተኛ ዓመት መታሰቢያ በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋካልቲ እሸቱ ጮሌ አዳራሽ ተካሂዷል።

🏃‍♂ በለንደን የወንዶች ማራቶን ውድድር ኬንያዊው አሞስ ኪፕሩቶ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶችን በማስከተል የርቀቱ አሸናፊ ሆኗል። በለንደን ማራቶን ተጠብቆ የነበረው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ #አምስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል።

🏃‍♀ በለንደን የሴቶች ማራቶን ውድድር የ23ዓመቷ ያለምዘርፍ የኋላው የለንደን ማራቶንን ሶስተኛውን የውድድሩ #ፈጣን_ሰዓት በማስመዝገብ በበላይነት ማጠናቀቅ ችላለች። የ23 ዓመቷ ያለምዘርፍ የኋላው የለንደን ማራቶን ማሸነፍ የቻለች ወጣት አትሌት መሆን ችላለች። በርቀቱ የተካፈለችው ሌላኛው አትሌታችን አለሙ መገርቱ ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች።

😢 በኢንዶኔዥያ በተደረገ የሀገሪቱ ትልቁ ደርቢ ጨዋታ ላይ በተፈጠረ ግጭት 127 ደጋፊዎች ህይወታቸው ማለፉ ተገልጿል። የተቀናቃኞቹ አሬማ እና ፐርሴብያ ጨዋታ በአሬማ የ3 ለ 2 አሸናፊነት ቀተጠናቀቀ በኋላ ነው ግጭቱ የተፈጠረው። ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ ከመጠቀም አንስቶ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዱ ነው የተገለጸው። በዚህ ምክንያት የኢንዶኔዥያ እግር ኳስ ማህበር ጉዳዩን እንደሚመረምርና ሊጉ ለአንድ ሳምንታት እንደተቋረጠ አሳውቋል።

#TikvahEthiopia

@tikvahethmagazine
#የዛሬ (መስከረም 23/2015)

📝 የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሄራዊ ፈተናን አስመልክቶ መግለጫ ተሰጥቷል።

በዚህም፦

- ከ900,000 በላይ ተማሪዎች የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሄራዊ ፈተናን የሚወስዱ ይሆናል።

- በሁለት ዙር በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በሚሰጠው በዚህ ፈተና የማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች ከመስከረም 26-28 ወደሚፈተኑባቸው ዩንቨርሲቲዎች የሚያቀኑ ሲሆን የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ከጥቅምት 5 አስከ ጥቅምት 6 ወደ ዩንቨርሲቲዎች ይጓዛሉ።

- ተፈታኞች ተንቀሳቃሽ ስልኮችን እና ሌሎችም ስጋት ሊፈጥሩ የሚችሉ ቁሶችን መያዝ እንደማይችሉ ተጠቅሷል።

- በተጨማሪም ከሰላምና ፀጥታ ጋር ተያይዞ መፈተን የማይችሉና ከሀገር የወጡ የኮሚኒቲ ተማሪዎች በአጠቃላይ 56,000 ተማሪዎች ሲሆኑ በቀጣይ #ሁለተኛ ዙር ፈተና እንደሚዘጋጅላቸው ሚኒስቴሩ ጠቁሟል።

🇺🇸 አምባሳደር ማይክ ሐመር ከዛሬ ሰኞ ጀምሮ ወደ ኬንያ ፣ ደቡብ አፍሪካ እና #ኢትዮጵያ ጉዞ ያደርጋሉ።

- የአሜሪካ አፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር ከጥቅምት 3 እስከ ጥቅምት 18 ቀን 2022 ወደ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኢትዮጵያ እንዘሚጓዙ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ዛሬ አሳውቋል።

- ሐመር ወደ ቀጠናው የሚመለሱት በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ግጭት በአፋጣኝ እንዲቆምና በአፍሪካ ህብረት የሚመራ የሰላም ድርድር እንዲጀመር ለመደገፍ ነው ተብሏል።

📱 ኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል ኢንሹራንስ ሊጀምር ነው

- የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ት ፍሬህይወት ታምሩ እንደተናገሩት አገልግሎቱ ደንበኞች ከኩባንያው ጋር በሚገቡት ውል መሰረት የእጅ ስልካቸው በሚጠፋበት እና በሚበላሽበት ጊዜ የሚስተናገዱበት አሰራር ነው፡፡

- ኩባንያው ከዚህም በተጨማሪ ኢ-ሲም ፤ ቴሌ ድራይቭ ፤ ኮል ሲግኒቸር እና ሌሎች በርካታ ምርት እና አገልግሎቶችን ኩባንያው ለደንበኞቹ በበጀት አመቱ እንደሚያቀርብ አስረድተዋል፡፡

⚽️ ስፖርት

- የሴካፋ ከ 17ዓመት በታች ውድድር መካሄዱን ሲጀምር ዩጋንዳ በሰፊ የጎል ልዪነት ቡሩንዲን 4ለ0 በመርታት ከወዲሁ ምድቧን መምራት ጀምራለች። የኢትዮጵያ ከ 17ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከ ሶማሊያ አቻው ጋር ባደረገው ጨዋታ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት ተሸንፏል።

- የ2013ዓ.ም የሊጉ አሸናፊ ፋሲል ከነማ የውድድር ዘመኑን አዳማ ከተማን 2ለ1 በመርታት በድል ጀምረዋል። መቻልና ሀዲያ ሆሳዕና ያደረጉት ጨዋታ ደግሞ በመቻል 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

#TikvahEthiopia

@tikvahethmagazine
#የዛሬ (መስከረም 25/2015)

🕊 የአፍሪካ ኅብረት #የሰላም_ንግግሩን የሚመሩ አካላትን፤ ቀንና ስፍራን አሳውቆ የሰላም ውይይቱ እንዲጀመር ኦፊሴላዊ ጥሪ አቅርቧል። ይህንን አስመልክቶ የፌዴራል መንግስት በደቡብ አፍሪካ ከጥቅምት 18 ጀምሮ የተጠራውን የሰላም ድርድር መቀበሉን በይፋ ሲያሳውቅ ህወሓትም በዚሁ ድርድር ላይ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን ዛሬ ምሽት አሳውቋል። ህውሓት ተጨማሪ ተዋናዮች ዝርዝር፣ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሚና እንዲሁም የሎጅስቲክስ ፤ የጉዞ እና የደህንነት ዝግጅቶችን በተመለከተ ማብራሪያ እኝዲሰጠው ጠይቋል።

💬 "ወላጆች የልጆቻችሁን ጉዳይ በሚመለከት በቀጥታ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር፤ የምንነግራችሁ ቁጥሮች አሉ፣ የምንልካቸው የአካባቢው ትምህርት ተወካዮች አሉ በዛ በኩል መገናኘት ያስፈልጋል። አንድ ነገር ቢፈጠር #በእርግጠኝነት የምንነግራችሁ ፤ ከእኛ ውሸት አትጠብቁ የሆነውን ነገር ይሄ ነው የሆነው ብለን እንነግራችኃለን። ምንም የምንደብቅበት ምክንያት የለም።" ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ (የትምህርት ሚኒስትር) ለብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ከተናገሩት የተወሰደ

🇰🇪 የኬንያ ፕሬዜዳንት ዶ/ር ዊሊያም ሩቶ የመጀመሪያ የአፍሪካ ሀገር ጉዟቸውን ወደ #ኢትዮጵያ ያደርጋሉ። ፕረዚደንቱ ነገ በአዲስ አበባ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ የቴሌኮም አገልግሎት ማስጀመሪያ ስነስርዓት ላይ እንደሚታደሙ የተነገረ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጋር ይመክራሉ ተብሏል።

💐 በአዲስ አበባ ትናንት ምሽት ከሌሊቱ 10:00 አካባቢ ባልታወቀ ምክንያት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 ልዩ ቦታው ወንጌላዊት አካባቢ በተፈጠረ የመሬት መደርመስ በደረሰ የመሬት መደርመስ የሁለት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በሌሎች ሁለት ሰዎች ላይ መጠነኛ ጉዳት በመድረሱ በህክምና እየተረዱ ይገኛሉ ተብሏል።

#TikvahEthiopia

@tikvahethmagazine
#የዛሬ (መስከረም 26/2015)

📝 በወጣላቸው የጉዞ መርሃ - ግብር መሰረት ለፈተና ወደየተመደቡባቸው ዩኒቨርስቲዎች እየተሸኙ ይገኛሉ። ከዚህ ባለፈም ፤ ሰኞ መስከረም 30 ለሚጀምረው ፈተና ተማሪዎች ወደፈተና ማዕከሎቻቸው እየገቡ ሲሆን በሚገቡበት ተቋም እንዲሁም ከመነሻቸው የፀጥታ አካላት ፍተሻ እያደረጉ ይገኛሉ።

4⃣📶 ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ አገልግሎት መጀመሩን ዛሬ አሳውቋል። ኩባንያው እስካሁን በ8 ከተሞች ከሁለት ቀናት በፊት በነበረ መረጃ ወደ 200 ሺህ ደንበኞች አፍርቻለው ብሏል።

📲 የኬንያው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዊልያም ሩቶ ሀገር አቀፍ የሳፋሪኮም የቴሌኮም አገልግሎት ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት ላይ በታደሙበት ዝግጅት የኢትዮጵያ መንግስት ለሳፋሪኮም የሞባይል ገንዘብ ዝውውር እንዲያደርግ መፈቀዱ ተገልጿል። ዛሬ ጠዋት ለሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ የገቡት ፕሬዜዳንቱ የኢትዮጵያ የስራ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ ኬንያ አመሻሹን ተመልሰዋል።

‼️ ኢሰመኮ በጋምቤላ ክልል፣ ጋምቤላ ከተማ ያካሄደውን የምርመራ ሪፖርት ማድረጉን ተከትሎ መስከረም 25 ቀን 2015 ዓ/ም በቡድን ሆነው የመጡ ሰዎች ወደ ኢሰመኮ ጋምቤላ ጽሕፈት ቤት በመሄድ የተለያዩ የጥፋት ድርጊቶችን መፈጸማቸውንና በኢሰመኮ ባልደረቦች ላይ #ዛቻ እና #ማስፈራሪያ ማድረሳቸውን ተቋሙ ገልጿል። ይህ ጥቃት በክልሉ የስብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ምልከታ የሚጥል በመሆኑ የፌዴራል እና የክልሉ የጸጥታ አካላት በአፋጣኝ ሊያስቆሙ ይገባል ሲል አሳስቧል።

🇪🇹 የኢትዮጵያ ከ 17ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከ ታንዛኒያ አቻው ጋር ባደረገው ጨዋታ 2 ለ 3 በሆነ ውጤት ተሸንፏል።

#TikvahEthiopia

@tikvahethmagazine
#የዛሬ (መስከረም 27/2015)

💰 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ 391 የሚደርሱ ሕገወጥ የሐዋላ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች የባንክ ሂሳባቸው ታግዶ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል። በተጨማሪም ከተፈቀደው በላይ በቤት ውስጥ የብር ክምችት የሚያደርጉ፣ የሀሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን የሚሠሩና የሚያሠራጩ ፣ በህገወጥ መልኩ የሐዋላ አገልግሎት የሚሠጡ ወይም በጥቁር ገበያ ላይ የተሰማሩ አካላትን ለሚጠቁሙ ዜጎች የወሮታ አከፋፈል ስርዓት ተዘጋጅቷል ብለዋል።

❗️ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ጭኖ ወደ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሲጓዝ የነበረ የህዝብ ተሽከርካሪ ትላንትና ሀሙስ በሰሜን ሜጫ ወረዳ በ " አምቦ መስክ " ቀበሌ የትራፊክ አደጋ የደረሰ ቢሆንም በተማሪዎች ላይ ምንም አይነት ጉዳት አላደረሰም ተብሏል። ተማሪዎቹ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስባቸው ሌላ መኪና ተቀይሮላቸው በሰላም ወደተመደቡበት መግባታቸው ነው ተለገለጸው።

❗️ ዛሬ በጅማ ዞን ፤ ከሲግሞ ወረዳ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎችን ጭኖ ወደ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ስጓዝ የነበረ አውቶብስ ተገልብጦ የትራፊክ አደጋ ደርሶ ነበር። ነገር ግን ተማሪዎች ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው መትረፋቸውን የወረዳው አስተዳደር አሳውቋል። የተማሪ ወላጆችም ይህንን በማወቅ እንዲረጋጉ መልዕክት ተላልፏል።

⚪️ በደቡብ አፍሪካ ነገ ሊጀመር የነበረው የሰላም ንግግር በሎጅስቲክስ ምክንያት መራዘሙን የዲፕሎማቲክ ምንጮች መግለፃቸውን ሮይተርስ ዘግቧል። ይህ ውይይት መቼ ይደረጋል የሚለው እስካሁን ቀን አልተቆረጠለትም። በተያያዘም የሰላም ንግግሩን እንደሚመሩ የተነገረላቸው አንዱ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ነገ በደቡብ አፍሪካ ይጀመራል ተብሎ በነበረው የሰላም ንግግር መድረክ ላይ በተመሳሳይ ቀን የያዙት ሥራ ስላለ እንደማይገኙ ገልጸዋል። ኬንያታ ሌላ የንግግር ቀን እስኪወሰን ድረስ ፣ ኅብረቱ ስለ ሰላም ንግግሩ ቅርጽ፣ አካሄድና አወያዮች መከተል ስላለባቸው ደንቦች ዝርዝር ማብራሪያ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል።

🏆 የ2022 የኖቤል የሰላም ሽልማትን ቤላሩስያዊው አክቲቪስት አሌስ ቢያሊያትስኪ፣ የዩክሬን የሲቪል ነፃነት ማዕከል እና የሩሲያ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት መታሰቢያ በጋራ አሸንፈዋል። ሦስቱ የኖቤል አሸናፊዎች የአልፍሬድ ኖቤል ሞት መታሰቢያ በሆነው ታኅሣሥ 1 ቀን 2015 በሚካሄደው ሥነ ሥርዓት ላይ በይፋ ሽልማታቸውን የሚወስዱ ይሆናል።

#TikvahEthiopia

@tikvahethmagazine