TIKVAH-ETHIOPIA
1.52M subscribers
59.5K photos
1.52K videos
215 files
4.13K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
加入频道
TIKVAH-ETHIOPIA
🔈#የጤናባለሙያዎችድምፅ " ከ15 ወራት በላይ የዱቲ ገንዘብ አልተከፈለንም በዚህ ኑሮ ውድነት በብድር በዬ ወሩ ተሰቃየን " - ጤና ባለሙያዎች በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፣ በጌዴኦ ዞን በዲላ ዙሪያ ወረዳ የሚገኙ ጤና ባለሙያዎች የ15 ቀናት የዘመቻ አበልና ከአንድ አመት በላይ የትርፍ ሰዓት ክፍያ ባለመፈጸሙ ችግር ላይ መሆናቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል። የጤና ባለሙያዎቹ ዝርዝር ቅሬታ ምንድን ነው…
🔈#የጤናባለሙያዎችድምጽ

🔵 " ቸግሮናልጠምቶናል፣ ርቦናል፣ ሰልችቶናል፣ ከኑሮ ውድነቱ ጋር ተያይዞ የዱቲ ሳይከፈለን ለ17 ወራት ስንሰራ ከመንግስት አካል ማንም ያሰበን የለም " - ጤና ባለሞያዎች

🔴 " ምንም ምላሽ የለንም። ቢሮ መጥተው ይጠይቁን " - ወናጎ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት

በጌዴኦ ዞን ወናጎ ወረዳ ያሉ ጤና ባለሙያዎች የወራት ያልተከፈለ የዱቲ ክፍያ እንዲፈጸምላቸው በመጠየቃቸው ከደመወዛቸው እንዲቆረጥባቸው መወሰኑን በመግለጽ በቲክቫህ ኢትዮጵያ በኩል ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

" ዱቲ ስላልከፈሉን የሰራነውን ገንዘብ ስለጠየቅን ብቻ ከሦስት ወራት በላይ ደሞዛችን ከ960 ብር ጀምሮ በስኬል  እየተቆረጠ ይገኛል " ብለው፣ ደመወዛቸው እንዲቆረጥ የተወሰነው የዱቲ ሥራ በማቆማቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የዱቲ ሥራ በመቆሙ ህዝቡም ችግር ላይ ስለሆነ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀው፣ " ካልሆነ ለሚፈጠር ችግር ተጠያቂ አንሆንም " ሲሉ አስጠይቅቀዋል።

በዞኑ ዲላ ዙሪያ ወረዳ ጪጩ ጤና ጣቢያ ያሉ ባለሙያዎቹ በበኩላቸው፣ የ17 ወራት የዱቲ ክፍያ እንዳልተፈጸመላቸው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

ያማረራቸውን ቅሬታ በተመለከተ በዝርዝር ምን አሉ ?

" በጌዴኦ ዞን በዲላ ዙሪያ ወረዳ የ17 ወራት የዱቲ ክፍያ ባለመከፈሉ የጪጩ ጤና ጣቢያ ከመስከረም 1 ቀን 2017 ዓ/ም ጀምሮ የዱቲ ሥራ በማቆም ሕዝቡ ከፍተኛ ችግር ላይ ወድቋል።

በተደጋጋሚ ለዞኑና ለወረዳው ቅሬታ ብናቀርብም ምላሽ በመስጠት ፈንታ ባለሞያዎችን ለእስር ሲዳርግ ቆይቷል። ለሦስት ዓመት ያክል በዱቲ ክፍያ እየተከራተተ የሚገኝ የዲላ ዙሪያ ወረዳ ጤና ባለሞያ እስከ ዛሬ ተገቢ ምላሽ አላገኘም።

በጌዴኦ ዞን በወናጎ ወረዳ የሚገኙ ጤና ባለሞያዎች የዱቲ ጥያቄ አቅርበው ተገቢ ምላሽ ባለማግኘታቸው መብታቸው ለማስከበር የዱቲ ሥራ በማቆማቸው በየወሩ ከደሞዛዝ እንዲቆረጥ ተወስኗል።

ዱቲ ስላልከፈሉን የሰራነውን ገንዘብ ስለጠየቅን ብቻ ከሦስት ወር በላይ ደሞዛችን ከ960 ብር ጀምሮ በየወሩ እየተቆረጠ ይገኛል። መንግስት አፋጣኝ ምላሽ ይስጠን።

ቸግሮናል፣ ጠምቶናል፣ ርቦናል ሰልችቶናል ሞራላችን ተነክቷል መውጫ ቀዳዳ አሳጥቶናል ከኑሮ ውድነት ጋር የዱቲ ሳይከፈለን ለ17 ወራት ስንሰራ ከመንግስት አካል ማንም ያሰበን የለም " ብለዋል።


ቲክቫህ ኢትዮጵያ ምላሽ የጠየቀው የወናጎ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ቀጥተኛ ማብራሪያ በመስጠት ፋንታ፣ " ምንም ምላሽ የለንም። ቢሮ መጥተው ይጠይቁን " ብሏል።

ሰሞኑን በተደጋጋሚ ስልክ ለማሳት ፈቃደኛ ባይሆኑም የጌዴኦ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አንዱዓለም ማሞ ከዚህ ቀደም ጉዳዩን በተመለከተ በሰጡትን ምላሽ ችግሩን ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑን ገልጸውልን ነበር።

"ጉዳዩ በእርግጥ ያለ ነው። መሠረታዊ ችግሩ የበጀት ችግር ነው፤ የካሽ እጥረት ነው ያለው። ያን ለመፍታት በጋራ እየሰራን ነው" የሚል ቃል ነበር የሰጡን።

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
Please open Telegram to view this post
VIEW IN TELEGRAM
🔈 #የጤናባለሙያዎችድምጽ

🚨“ የሐምሌ 2016 ዓ/ም ደመወዝና፣ የ23 ወራት የዱቲ ክፍያ ስላልተከፈለን የዱቲ ሥራ ለማቆም ተገደናል” - የሀላለ ሆስፒታል ጤና ባለሞያዎች

🔴 “ የ23 ወራት ባይሆንም የ20 ወራት የዱቲ ክፍያ አልተከፈላቸውም ” - ሆስፒታሉ

🔵 “ የአንድ ወይም ሁለት ወራት እንጂ የዚህን ያክል የተወዘፈ ክፍያ የለም ” - የወላይታ ዞን ጤና መምሪያ

በወላይታ ዞን ኪንዶ ዲዳዬ ወረዳ ሀላለ ሆስፒታል የሚገኙ 78 ጤና ባለሞያዎችና ሌሎች ሠራተኞች የአንድ ወር ደመወዝና የ3 ዓመት የዱቲ ክፍያ ስላልተከፈላቸው የትርፍ ሰዓቱን ሥራ ለማቆም መገደዳቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናገሩ።

ጤና ባለሞያዎቹ በሰጡን ቃል ምን አሉ?

“መንግስት ከሚመድበው በጀት ክፈሉ ብለን በደብዳቤ ብንጠይቅም ‘እንከፍላለን አሁን ግን የካሽ እጥረት አለብን’ አሉን። ከዚህ ባለፈ ማስፈራሪያ፣ እስራት፣ ድብደባ ይደርስብናል።

የመጀመሪያ የስምነት ወራት የዱቲ ክፍያ በተመለከተ ተካስሰን ፍርድ ቤት እንዲከፈለን ውሳኔ ቢሰጠንም በፖለቲካ ሰዎች ጣልቃ ገብነት ውሳኔ ባለመከበሩ አልተከፈለንም።
 
ከዚያ ወዲህ የሰራነውን የ15 ወራት የትርፍ ሰዓት ክፍያንም ቢሆን ባለመክፈላቸው፣ ለመክፈልም ፍላጎት የሌላቸው በመሆኑ ከሆስፒታሉ ሠራተኞች ኃላፊ ውጪ በአጠቃላይ ተፈራሪመን የትርፍ ሰዓት ሥራ ለማቆም ተገደናል።

በደላችንን፣ ድምፃችንን ለህዝብ እና ለመንግስት አሰሙልን። ጤና ሚንስቴር በህይወት ካለ መብታችንን ያስከብርልን” ሲሉ አሳስበዋል።


ቲክቫህ ኢትዮጵያ፣ የአንድ ወር ደመወዝና የ23 ወራት ወራት የትርፍ ሰዓት ክፍያ ያልተፈጸመበት ምክንያት ምንድን ነው? ሲል ለሆስፒታሉ ጥያቄ አቅርቧል።

የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ በረከት ሌራ ምን ምላሽ ሰጡ?

“የኛ ተቋም የሚያስተዳድረው ገንዘብ የለም ስራዎች ከተሰሩ በኋላ ለወረዳ ፋይናንስ ሪፓርት ቀርቦ ያንን መሠረት በማድረግ ነው ክፍያ የሚፈጸመው። 

የ2016 ዓ/ም የሐምሌ ደመወዝ 13% ብቻ ነው የሚቀረው 87% ተከፍሏል። የ23 ወራት ባይሆንም የ20 ወራት የትርፍ ሰዓት ክፍያ አልተከፈላቸውም። ሰፊ ነው ችግሩ። የካሽ እጥረት በሚል ብዙ ነገር እየተባለ ነበር።

የዱቲ ክፍያ በተመለከተ ፍርድ ቤት ክፍያ እንዲፈጸም የሚል ውሳኔ ሰጥቷል። የወረዳው መንግስት ከክስ ሂደቱ በኋላ መክፈል ከጀመረ በኋላ ነው የቆመው።

‘በንግግር ችግሮችን እየፈታን እንመጣለን’ በሚል ቃል ከተገባልን በኋላ ነው በመካከል ክፍያው የቆመው።  የሚያዚያ ወር በከፊል መከፈል ከተጀመረ በኋላ ነው ቆመ”
ብለዋል።

የዱቲ ሥራ በመቆሙ በማታ የሚመጡ ወላድ እናቶችን ብቻቸውን እያከሙ መሆኑን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡ አሳስበዋል።

ባለሙያዎቹ የ23 ወራት የዱቲ ክፍያ እንዳልተፈጸመላቸው ቅሬታ አቅርበዋል፣ ሆስፒታሉም የ20 ወራት የዱቲ፣ የሐምሌ ደመወዝ 13 በመቶ ክፍያ አለመፈጸሙን ገልጿል፣ ይህ ለምን ሆነ? ጉዳዩን ተመልክታችሁት ነበር? ስንል ለወላይታ ዞን ጤና መምሪያ ጥያቄ አቅርበናል።

የወላይታ ዞን ጤና መምሪያ ምን አለ?

የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ፀጋዬ ኤካ፣ “የ23 ወራት እንዳልተከፈለ መረጃው የለኝም። ተከፍሎ ነው እየተሰራ ያለው። ትክክል ነው ለማለት እቸገራለሁ” ሲሉ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ምላሽ ሰጥተዋል።

የ20 ወራት የዱቲ ክፍያ እንዳልተከፈላቸው ሆስፒታሉም እንዳረጋገጠ ስንገልጽላቸውም፣ “20 ወራት አይደርስም እኔ እንደማውቀው። ማጣራት ይጠይቃል” ነው ያሉት።

“የአንድ ወይም ሁለት ወራት እንጂ የዚህን ያክል የተወዘፈ ክፍያ የለም” ያሉት ኃላፊው፣ ጉዳዩን አጣርተው ተጨማሪ ማብራሪያ ለመስጠት ቃል ገብተዋል።

ሆስፒታሉ ያልተከፈላችሁ የ20 ወራት የዱቲ ክፍያ መሆኑን ገልጿል፣ እናንተ ደግሞ ያልተከፈላችሁ የ23 ወራት እንደሆነ ገልጻችኋል ፣ የትኛው ነው ትክክል ? ስንል የጠየቅናቸው ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል።

“ ከ23 ወራት የዱቲ የ3 ወሯን ለተወሰኑ ሰዎች ነበር የከፈሉት። በትምህርት፣ በዝውዝውር፣ ሥራ በመልቀቅ ሄዱት ሳይከፊሉ ነው ‘ከፍለናል’ የሚሉት ነገር ግን እነዚህ ባለሙያዎች ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ህብረተሰቡን እንዳገለገሉ መረሳት አልነበረበትም ” ነው ያሉት።

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
Please open Telegram to view this post
VIEW IN TELEGRAM
🔈 #የጤናባለሙያዎችድምጽ

“ ማንም መልስ የሰጠን የለም። ችግሮቹም ከቀን ወደ ቀን እየተባበሱ ነው ” - የኢትዮጵያ ህክምና ማኀበር

የኢትዮጵያ ህክምና ማኀበር፣ “ በተለያዩ በሽታዎች ተይዘው ከፍተኛ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ሀኪሞቻችን ተገቢውን ህክምና በፍጥነት ባለማግኘታቸው የህይወት ዋጋ እየከፈሉ ይገኛሉ ” ሲል ወቅሷል።

ማኀበሩ ይህን ያለው፣ ከየካቲት 14 እስከ 15 ቀን 2017 ዓ/ም ስለሚያካሂደው 61ኛው ዓመታዊ የህክምና ጉባዔ በተመለከተ ዛሬ በሰጠው መግለጫ ነው።

ጉባኤው፣ “ በኢትዮጵያ የሚገኙ ጤና ባለሙያዎች ደህንነት አሁናዊ ሁኔታና አማራጭ መፍትሄዎች ” በሚል መሪ ቃል እንደሚካሄድ አመልክቷል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያም ስለሀኪሞች ህክምና የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ምን እንደሚመስል፣ ለኢትዮጵያ ሀኪሞች ምን መደረግ እንዳለበት ማኀበሩን ማብራሪያ ጠይቋል።

የማኀበሩ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ትዕግስት፣ በሰጡት ምላሽ “ በብዛት በኢንሹራስ ከቨር የሚደረግበት ሁኔታ አለ በጥናት የተደገፈ መረጃ ባይኖርም የሌሎች አገራትን ተሞክሮ በተመለከተ ” ብለዋል።

አክለው፣ “ የኛ አገርን በተመለከተ የኢንሹራንስ ከቨርም ስለማይደረግ ጤና ባለሙያዎች እንደማናቸውም ማኀበረሰብ በትንሽ በሀገር ታክመው የማይዳኑ በጣም የተወሳሰቡ ህመሞች ሲታመሙ እናያለን ” ነው ያሉት።

ተመሳሳይ ጥያቄ ያቀረብንላቸው የማኀበሩ የቦርድ አባል ዶ/ር በሀሩ በዛብህ ፣ “ ችግሩ የቆዬ ነው። ማንም መልስ የሰጠን የለም። ችግሮቹም ከቀን ወደ ቀን እየተባበሱ ነው ” ሲሉ መልሰዋል።

ዶ/ር በሀሩ በዛብህ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል በዝርዝር ምን አሉ ?

“ ለሀኪሞች የኢንሹራንስ ከለላ መኖር አለበት። ራሳችን ያመጣነው በሽታ እንኳ ሳይሆን ስናክም ብዙ በሽታዎችን ነው የምናገኘው። ብዙ የጤና ባለሙያዎች በህክምና ሂደት ላይ ግራጁዋሊ በሚያገኙት በሽታ ሞተዋል።

ክብደት ያለውን ታካሚ እያነሳ የአካል ጉዳተኛ የሚሆንም አለ። ከተላላፊ በሽታዎች ጋር እንሰራለን። ስለዚህ ጤና ባለሙያዎች በእነዚህ በሽታዎች ይጎዳሉ።

ብዙዎች እንደዚህ አይነት ችግሮች መኖራቸውን ሲያውቁ ሙያቸውን ሁሉ የቀየሩ አሉ። ወጣቶች ትምርታቸውን አቋርጠው ወደ ሌላ ሙያ የሚሄዱበት ሁኔም አለ።

ለሀኪሞች ተላላፊ የሆነ በሽታ መከላከያ ሂደቶች የሉም። መካላከያ ኖሮም በሽታ የሚተላለፍበት ሁኔታ አለ። ግን ለማገገም የሚሰጥ ህክሞና የለም። 

አንዳንድ መከላከያዎች ውድ ናቸው። ያን ለማቅረብም የኢኮኖሚው ሁኔታ ያን ያክል አይፈቅድም”
ብለዋል።

በሌላ በኩል፣ ሀኪሞች ብዙ ጭናዎችን ተቋቁመው እየሰሩ የሰሩትን የዲዩቲ ክፍያ እንዲፈጸምላቸው ሲጠይቁ ለእስር ሲዳረጉ መስተዋሉን የገለጸው ማኀበሩ፣ በጉባዔው ወቅት ውይይት እንደሚደረግበት ጠቁሟል።

(የማኀበሩ ሙሉ መግለጫ ከላይ ተያይዟል)

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
Please open Telegram to view this post
VIEW IN TELEGRAM
🔊 #የጤናባለሙያዎችድምጽ

🔴
የጸጥታ አካላት ሆስፒታል ድረስ በመምጣት ድብደባ ፈጽመዋል፣ ዘጠኝ ሠራተኞችና የማኔጅመንት አባላትን አስረዋል ” - የሆስፒታሉ ሠራተኞች

➡️ “ እነርሱ ጋ ብቻ አይደለም ያልተከፈለው፤ ከ2000 በላይ ሠራተኞች እንደ ዞን ያልተከፈላቸው አሉ ”  - የጌዴኦ ዞን ጤና መምሪያ

በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ከተማ፣ የይርጋጨፌ ሆስፒታል ጤና ባለሙያዎችና የአስተዳደር ባለሙያዎች “ በጸጥታ አካላት ድብደባና እስራት ተፈጽሞባቸዋል ” ሲሉ ሠራተኞቱ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናገሩ።

ተፈጽሟል ስላሉት እስራትና ድብደባ ምክንያት ምን እንደሆነ ሲገልጹ፣ እንደ ሀገር የተደረገው የደመወዝ ጭማሪ ክፍያ ባለመፈጸሙ የሥራ ማቆም አድማ መደረጉን ተከትሎ መሆኑን ሠራተኞቹ አስረድተዋል።

የአራት ወራት የደመወዝ ጭማሪ ክፍያ ከ150 በላይ ለሚሆኑ የሆስፒታሉ ሠራተኞች አለመፈጸሙን፣ እስከ የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ/ም እንዲፈጸምላቸውና እስከተጠቀሰው ጊዜ ድረስ ካልተፈጸመላቸው ሥራ የማቆም አድማ ለማድረግ እንደሚገደዱ በደብዳቤ ጭምር ማሳወቃቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም ክፍያው ባለመፈጸሙ የሥራ ማቆም አድማ እንዳደረጉ፣ የተወሰኑት ሥራ ማቆም አድማ ያላደረጉ ሰራተኞች ቢሮ ባሉበት “ አድማ አስመትታችኋል ” በሚል እስራትና ድብደባ እንደተፈጸመባቸው በመግለጽ አማረዋል።

በዚህም፣ “የካቲት 10 እና 11 ቀን 2017 ዓ/ም ሥራ አልገባንም። በቀን 12/2017 ዓ/ም ደግሞ ሙሉ ፓትሮል ፓሊስ መጥቶ በሥራ ላይ የነበሩ የማኔጅመንት አባላትን ይዘው ወጡ ” በማለት ተናግረዋል።

አክለው፣ “ ከየቤቱ ያሉት ሠራተኞችም መረጃው ደርሷቸው ‘ካሰራችሁ ሁላችንንም እሰሩን የሁላችንም ጉዳይ ነው’ ብለው እስሩ ከተፈጸመበት ፓሊስ ጣቢያ ድረስ ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተዋል ” ሲሉ ሁነቱን አስረድተዋል።

የታሰሩት ምን ያክል ግለሰቦች ናቸው? ስንል የጠየቅናቸው ሠራተኞቹ በሰጡት ምላሽ፣ “የታሰሩት የሆስፓታሉ ሠራተኞችና የማኔጅመንት አባላት ናቸው፡፡ የጸጥታ አካላት ሆስፒታል ድረስ በመምጣት ድብደባ ፈጽመዋል፣ 9 ሠራተኞችና የማኔጅመንት አባላትን አስረዋል ” ብለዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ የሠራተኞቹን ቅሬታ በመያዝ፣ ድርጊቱ ለምን እንደተፈጸመ የጌዴኦ ዞን ጤና መምሪያ ቢሮን ምላሽ የጠየቀ ሲሆን፣ እስራቱ መፈጸሙን እና ደመወዙ አለመከፈሉን አምኖ ምላሽ ያለውን ሰጥቷል።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ አንዱዓለም ማሞ በዝርዝር ምን መለሱ ?

“ ባለሙያዎቹ የካቲት 7 መጥተው ነበር። ከኛ ጋ ውይይት አድርገዋል፡፡ ውይይት ካደረግን በኋላ ፕሮሰስ እያደረግን ለማክሰኞ ጠዋት ክልል ቀጠሮ እንደነበረ ገልጸንላቸው ነበር፡፡ ማክሰኞ ሂደን ዘጠኝ ሰዓት ላይ ምላሽ ታገኛላችሁ ብለናቸው ነበር፡፡

እነሱ ጋ ብቻ አይደለም ክፍያው ያልተከፈለው ከ2000 በላይ ሰራተኞች እንደ ዞን ያልተከፈላቸው አሉ፡፡ እንደ ዞንም ሶስት ሆስፒታል ላይ ነው ክፍያው ያልተከፈለው፡፡ የተለያዩ የጤና ባለሙያዎችም በወረዳ ደረጃ ያልተከፈላቸው አሉ፡፡

በሦስቱ ሆስፒታሎች ነው ያልተፈጸመው። ግን ሁለቱ ሆስፒታሎች የስራ ማቆም አድማ አላደረጉም፡፡ እነርሱ ግን ለማክሰኞ ቀጥረናቸው እያለ ቀጠሮውን አንቀበልም ብለው ሙያዊ ሥነ ምግባር በማይፈቅድ መንገድ ስራ የማመጽ ነገር አድርገው ነበር።

ግን የተወሰኑ ልጆች ደግሞ ስራ ገበታ ላይ ተገኝተው ነበር፡፡ ስለዚህ ኦሬዲ ድስከስ አድርገን ጉዳዩን ፈተን ልጆቹ ስራ ጀምረዋል አሁን፡፡ ስራ ላይ ናቸው ሁሉም ” ብለዋል።

ታሰሩ የተባሉት የሆስፒታሉ ባልደረቦች ሳይፈቱ እንዴት ሁሉም ስራ ላይ ሊገኙ እንደቻሉ ምላሽ የጠይቅናቸው ኃላፊው፣ “እነርሱ ያልተገባ አካሄድ የሄዱ አሉ፡፡ ከስነ ስርዓት ውጭ ያልተፈቀደ ሰልፍ የወጡበት ሂደትም አለ፡፡ እንግዲህ ከእስር እንዲወጡ እየተሰራ ያለበት ሂደት አለ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ሠራተኞቹ ቅሬታ ያቀረቡት የአራት ወራት ገደማ ደመወዝ አለመጨመሩን ተከትሎ ነውና የመብት ጥያቄ በመቅረቡ እስርና ድብደባ መፈጸም አግባብ ነው? ሲል ቲክቫህ ኢትዮጵያ ተጨማሪ ጥያቄ አቅርቧል።

አቶ አንዷለም በሰጡት ማብራሪያ፣ “ሠራተኞቹና ባለሙያዎቹ፣ ‘የፈጸምናቸው ድርጊቶች ትክክል አይደሉም ህዝቡን በድለናል ብለው’ ይቅርታ ጠይቀው ወደ ስራ ገብተዋል፡፡ ከአጠቃላይ ሰራተኞች ውይይት ተደርጎ ጤናማ ስራ ጀምረዋል አሁን” ሲሉ አስተባብለዋል።

ይቅርታ የጠየቁት ማን ናቸው? ሰራተኞቹ ወይስ አሳሪዎቹ? ስንል ላቀረብነው ጥያቄም  ኃላፊው፣ “ሰራተኞቹ ” ሲል የመለሰ ሲሆን፣ ታስረው እያለ እንዴት ይቅርታ ይጠይቃሉ? ሲል ቲክቫህ ኢትዮጵያ በድጋሚ ጥያቄ አቅርቧል።

እሳቸውም፣ “ሙያዊ ክብር በጣሰ መልኩ ሰልፍ የወጡትም ይቅርታ እየጠየቁ ነው ያሉት አሁን፡፡ ‘እነርሱ ናቸው ጥፋተኛ’ በሚል ልከውልናል ቤተሰቦቻቸው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የተወሰኑት ሠራተኞች የስራ ማቆም አድማ አድርገው ነበር፤ በአንጻሩ ደግሞ የተወሰኑት ደግሞ ስራ ላይ ተገኝተው ነበር፤ ነገርግን ‘ሌሎቹን አሳምጻችኋል’ በሚል ስራ የገቡትም ናቸው የታሰሩት። ሥራ ላይ እያሉ ታስረው ሳለ “ይቅርታ ጠይቀዋል” መባሉ ምን ማለት እንደሆም በድጋሚ ምላሽ ጠይቀናል።

አቶ አንዷለም በምላሻቸው፣ “ነገሩ እንግዲህ እንደዚሁ ነው። አሁን ውይይት ላይ ነን፡፡ እነርሱ የሰሩት ጥፋት ስለነበረ ነው የተጠየቁት። አሁን ይቅርታ ጠይቀው ውይይት ላይ ነን ችግሩን ለመፍታት” ነው ያሉት፡፡

እንዳጠቃላይ ችግሩን ለመፍታትስ ምን እየተሰራ ነው? ስንል ላቀረብነው ጥያቄም፣ “አሁን በጀቱ እውቅና አግኝቷል፡፡ ለሰራተኞች የጸደቀላቸው በጀት እጃችን ላይ ገብቷል፡፡ የክፍያ ሂደት ለማመቻቸት ጥረት እየተደረገ ነው” ብለዋል።

“ከክልል ፋይናንስ ገንዘብ እንድለቀቅ ሂደት ላይ እንደሆነና ያው ከዚያ እንደተለቀቀ ክፍያ እንደሚከፈል ተግባቦት ላይ ተደርሷል” ሲሉም አክለዋል፡፡

(ጉዳዩን እስከመጨረሻ የምንከታተለው ይሆናል)

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia