TIKVAH-ETHIOPIA
1.52M subscribers
59.6K photos
1.52K videos
215 files
4.14K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
加入频道
"በኢትዮጵያ 27 በመቶ ያህል ሰዎች #የአዕምሮ ጤና ችግር አለባቸው።" ዶክተር #ዳዊት_አሰፋ (የኢትዮጵያ አዕምሮ ህክምና ማህበር ፕሬዝዳንት)

@tsegabwolde @tikvahethiopia
"በኢትዮጵያ 27 በመቶ ያህል ሰዎች #የአዕምሮ ጤና ችግር አለባቸው።" ዶክተር #ዳዊት_አሰፋ (የኢትዮጵያ አዕምሮ ህክምና ማህበር ፕሬዝዳንት)
.
.
በአዕምሮ ጤና ህክምና ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በቅንጅት #ለመፍታት አገራዊ የአዕምሮ ጤና ኢንስቲትዩት የማቋቋም ተግባር ሊፋጠን እንደሚገባ ተገለፀ።

የኢትዮጵያ አዕምሮ ህክምና ማህበር ከአፍሪካና ከአለም አቻው ጋር በመሆን ያዘጋጀው ለሶስት ቀን የሚቆይ ምክክር ትላንት ተጀምሯል።

በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ አዕምሮ ህክምና ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳዊት አሰፋ ለኢዜአ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ 27 በመቶ ያህል ሰዎች የአዕምሮ ጤና ችግር አለባቸው።

ከነዚህም ውስጥ እስከ ሁለት በመቶ የሚሆኑት ከባድ የአዕምሮ ጤና ችግር ያለባቸው መሆናቸውንም ነው የገለፁት።

ኅብረተሰቡ ስለ አዕምሮ ጤና ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑን ያስረዱት ዶክተር ዳዊት ይህንንና በዘርፉ ያሉ ሌሎች እንደ ግብዓትና ተደራሽነት የመሳሰሉ ችግሮችን ለመፍታት ተቋማዊ አሰራርና አደረጃጀት ሊኖር ይገባል ብለዋል።

ችግሩን ለመፍታት አገራዊ የአዕምሮ ጤና ኢንስቲትዩት እንደሚያስፈልግ ተናግረው በዚህ ዙሪያ የተጀመሩ ስራዎች በመኖራቸው መንግስት ትኩረት በመስጠት በአጭር ጊዜ ውስጥ መጠናቀቅ እንዳለበትም ነው ያብራሩት።

በአዕምሮ ጤና ላይ በተናጥል መስራት ለውጥ ለማምጣት አያስችልም ያሉት ዶክተር ዳዊት አገራዊ የአዕምሮ ጤና ኢንስቲትዩት መኖር በቅንጅት ስራዎችን ለመስራት ያስችላል ነው ያሉት።

ተቋሙ በስልጠናና ምርምር እገዛ የሚፈጥር እንደሚሆንም ነው ያስረዱት።

ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚቀጥለው በአዕምሮ ጤና አገልግሎት ላይ የሚያተኩረው ምክክርም ተሞክሮን ለመቅሰምና ከሌሎች አቻ ተቋማት ጋር አጋርነት ለመፍጠር እንደሚረዳም ነው ዶክተር ዳዊት የተናገሩት።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው በአገሪቱ የአዕምሮ ጤና ህክምና እንዲሻሻል የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከማህበሩና ከአዕምሮ ጤና ባለሙያዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት መስራቱን እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

በዓለም ላይ ከአምስት ሰዎች አንዱ የአዕምሮ ጤና ችግር እንዳለበት በተለይ በድህነት ውስጥ የሚኖሩ፣ ስደተኞች፣ ለጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የተጋለጡ ሴቶችና ህፃናት ተጋላጭነታቸው የሰፋ መሆኑን ያስረዱት ደግሞ የዓለም የአዕምሮ ህክምና ማህበር ፕሬዝዳንት ሄለን ሄርማን ናቸው።

ማህበሩ በ120 የዓለም አገራት የሚሰራ መሆኑን ተናግረው የዛሬው መድረክም በአዕምሮ ጤና ላይ የተሰሩ ሳይንሳዊ መረጃዎችን ለመለዋወጥና እውቀቶችን ለመጋራት እንደሚረዳም ነው ፕሬዝዳንቷ የገለፁት።

እየተካሄደ ባለው ምክክር ላይ ከ70 በላይ ሳይንሳዊ ፅሁፎች የሚቀርቡ ሲሆን ከ30 የዓለም አገራት የተውጣጡ የአዕምሮ ጤና ባለሙያዎች እንደሚሳተፉም ለማወቅ ተችሏል።

በምክክሩ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውን ጨምሮ የአፍሪካ የአዕምሮ ህክምና ፕሬዝዳንትና ሌሎች የአዕምሮ ጤና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

ምንጭ፦ ኢዜአ
@tsegabwolde @tikvahethiopia