TIKVAH-ETHIOPIA
1.52M subscribers
59.6K photos
1.52K videos
215 files
4.14K links
ይህ የቲክቫህ (ተስፋ) ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት መሰባሰቢያ እንዲሁም የመረጃ እና የመልዕክት መለዋወጫ መድረክ ነው።

@tikvahuniversity
@tikvahethAfaanOromoo
@tikvahethmagazine
@tikvahethsport
@tikvahethiopiatigrigna

#ኢትዮጵያ
加入频道
“ብዙ ከእኛ ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ነገሮች ይኖራሉ። ነገር ግን ሁሉም ነገር በትክክል ከተካሄደ ሊበቃን ይችላል” - ምክትል ኮሚሽነር ሒሩት ገብረ ሥላሴ

ከቀናት በፊት አንድ አመት ተጨማሪ የሥራ ጊዜ በፓርላማ የተሰጠው የ3 አመታት የሥራ ዘመኑን ነገ ይጠናቅቅ የነበረው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የ3 አመታት ክንውንና የቀጣይ አቅጣጫውን በተመለከተ ዛሬ በስካይ ላይት ሆቴል መግለጫ ሰጥቷል።

በዚህም ኮሚሽኑ የተሰጠው ተጨማሪ ጊዜ በቂ ነው? አጠቃላይ ሥራውስ መቼ ይጠናቀቃል? በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረላቸው ጥያቄ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረ ስላሴ፣ “ብዙ ከእኛ ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ነገሮች ይኖራሉ። ነገር ግን ሁሉም ነገር በትክክል ከተካሄደ ሊበቃን ይችላል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

"ከእኛ ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ነገሮች አሉ” ያሉት፣ ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ይህን ይበሉ እንጂ ከቁጥጥር ውጪ ስለሆኑ ነገሮችን በዝርዝር አልገለጹም። 

11 ኮሚሽነሮች እንዳሉና ሥራውን ተባብሮ ለመስራት እንደሚቻል ገልጸው፣ "ተጨማሪ አንዳንድ ሥራዎችን የሚያቃልሉ ነገሮች በመንግስትም ሆነ በሌሎች ከተፈጠሩልን ስራችንን ያጣድፋል" ብለዋል።

“ምክክር በዚህ ሰዓት ውስጥ ተመካክራችሁ በዚህ ጊዜ ውስጥ ውሳኔ ስጡ የሚባልበት አይደለም። ህዝቦች ቁጭ ብለው ጊዜ ውስደው ተመካክረው የሚወሰኑት ሂደት ስለሆነ በቀላሉ የሚወሰኑ አጀንዳዎች ይኖራሉ። ጊዜ የሚፈጁም ሊኖሩ ይችላሉ” ሲሉም አስረድተዋል።

አክለው፣ “በዚህ ምክንያት በትክክል በዚህ ጊዜ ውስጥ ያልቃል ለማለት ያስቸግራል” ብለው፣ ሆኖም ግን ኮሚሽኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሥራውን ለመጨረስ ጥረት እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የተወሰኑ ፓርቲዎች ባልተሳተፉበት የምክክሩ ሂደቱ ሙሉ ይሆናል? በሚል ለቀረበው ጥያቄም፣ ፓርቲዎች በምክክሩ እንዲሳተፉ ጥረት መደረጉን ገልጸው፣ “ዳተኛ ሆነው” ያልገቡት እንዲገቡ ደግሞ ንግግር እንደተደረገ፣ አሁንም ጥረቱ እንደሚቀጥል አስረድተዋል። 

ዋና ኮሚሽነር መስፍን ዓርዓያ (ፕ/ር) በበኩላቸው፣ በመግለጫው ባደረጉት ንግግር በሕጋዊ ከተመዘገቡ ወደ 70 ፓርቲዎች 57 የሚሆኑት ከኮሚሽኑ ጋር እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ከታጣቂዎች ጋር ንግግር ተደርጎ እንደሆን ከጋዜጠኞች ጥያቄ ቀርቦላቸው በሰጡት ማብራሪያ ዋና ኮሚሽነሩ፣ የፋኖ ታጣቂዎችን እንዳነጋገሩ፣ “ሊከፋፍለን ነው” በሚል ስማቸው እንደሚነሳ አስታውሰው ተከታዩን ብለዋል።

ምን አሉ?

“ሀገራዊ ምክክሩ ማንንም መከፋፈል አይመኝም። የሚመኘው፣ መደረግ አለበት ብሎ የሚያምነውም ሁሉም ተሳታፊ እንዲሆን ነው።

እኔ ፋኖ መሆናቸውን አላውቅም አንድ ታጣቂ ቡድን ራሳቸው ደውለውልኝ ‘የምክክር ኮሚሽኑን ሥራ ተገንዝበናል። ‘በዚህ መሠረት ወደ ትግሉ የገባንበትን አጀንዳ ወደ እናንተ አምጥተን ወደ ውይይት የሚቀርብ ከሆነ መሳሪያችንን ለማስቀመጥ ዝግጁ ነን’ የሚል በቀጥታ በግሌ አቅርበውልኛል። ይሄን ሰው በተደጋጋሚ አግኝተዋለሁ። 

እዛ ላሉትም የደኅንነት፣ አካላት በስልክ አግኝቼ እነዚህ ሰዎች በአግባቡ መሠረት ሰላማዊ ጥበቃ ተደርጎላቸው አጀንዳቸውን የሚያመጡበት መንገድ እንዲመቻች ይሄን አስተላልፌያለሁ። 

ይህን ሳደርግ ለሀገራዊ ምክክር ጉባዔ በማሳወቅ ነው። እንጂ የፋኖ ናቸው ብዬ የተናገርኩት አንድም የለም” ብለዋል።

በሌላ በኩል በዛሬው መግለጫ የኮሚሽኑ የ3 አመታት ክንውኖች በኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን ዓርዓያ (ፕ/ር) በዝርዝር የቀረቡ ሲሆን፣ ይህንኑ ሪፓርት ከቀናት በፊት አድርሰናችሁ ነበር።

(ተጨማሪ ዘገባ በቀጣይ የምናቀርብ ይህናል)

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
#AddisAbaba 🚨" ባለፉት 6 ወራት ብቻ ከ1 ሚሊየን 293 ሺህ በላይ አሽከርካሪዎች በትራፊክ ፖሊስ አባላት ብቻ  ተቀጥተዋል !! " እንደ ሸገር ሬድዮ ዘገባ ፥ በአዲስ አበባ በየቀኑ በአማካይ 7,183 አሽከርካሪዎች በትራፊክ ደንብ መተላለፍ በትራፊክ ፖሊስ ብቻ ይቀጣሉ። ይህ በሌሎች የትራፊክ ደንብ ታላፊዎችን የሚቀጡትን አይጨምርም። ባለፉት በ6 ወራት ውስጥ በተለያዩ የደምብ መተላለፍ…
" አንዳንዴ ቀን ሙሉ የሰራነውን ገንዘብ ያለ አንዳች ጥፋት ተቀጥተን ባዶ እጃችንን ቤታችን እንገባለን ! " - አሽከርካሪዎች

በአዲስ አበባ በርካታ አሸከርካሪዎች ከትራፊክ ቁጥጥር ጋር በተያያዘ ወቀሳ እና ቅሬታ ያቀርባሉ።

ለአብነትም ፤ አንዳንድ የትራፊክ ፖሊስ አባላት ያለ አንዳች ምክንያት እየሄደ ያለን ተሽከርካሪ ማስቆም ፤ ጥፋት ሲያጡ ጥፋት ወደ መፈለግ መግባት ከዛ የቅጣት ወረቀት ላይ መፃፍ ስራቸው ያደረጉ አሉ።

ከዚህ ባለፈ ለዜጎች ክብርን ያለመስጠት ፤ ዝቅ ብሎ አለማገልገል፣ አሽከርካሪዎችን መናቅ ፣ ምንም የምታመጡት ነገር የለም ማለት፣ በስርዓት አለማናገር፣ ጥፋትን አለማስረዳት ... የመሳሰሉ ባህሪዎችም ይታይባቸዋል።

አንዳንድ ትራፊክ ፖሊስ አባላት የትራፊክ ሁኔታውን ማሳለጥ ሲገባቸው እንቅፋትም ይሆናሉ።

መሃል መንገድ ላይ፣ አደባባይ ላይ ሳይቀር የትራፊክ እንቅስቃሴን በሚያውክ መልኩ ተሽከርካሪ አስቁመው መንገድ እንዲዘጋጋም ያደርጋላ።

በተለያየ ጊዜ ቃላቸውን አሽከርካሪዎች ቁጥጥር መኖሩን ግዴታ ቢሆንም በአግባቡ እና በስርዓት መሄን እንዳሚገባው ያነሳሉ።

" ቅጣቱ ለተላለፈ ደንብ መቅጫ ሳይሆን ከዜጎች ገንዘብ መሰብሰቢያ ሆኗል " የሚሉት የሜትር ታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ አሽከርካሪዎች " ቀን ሙሉ የሰራነውን አንዳንዴ ያለ አንዳች ጥፋት ተቀጥተን ባዶ እጃችንን ቤታችን እንገባለን " ብለዋል።

" በተለይ የቅጣት ብሩ ከጨመረ ወዲህ በሆነው ባልሆነው መኪና እያስቆሙ መቅጣት ተበራክቷል " ሲሉም ገልጸዋል።

በተላይ አዳዲስ በተሰሩ የመንገድ ዳሮች ማቆም ስላማይቻል ስራቸውን ለመስራት እንደተቸገሩ ሆኖ ሳለ ያለ አግባብ በትራፊክ ፖሊስ እና የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የሚጣለው ቅጣት ቀን ሙሉ ለፍተው ማታ ባዶ እጃቸውን ወደ ቤት እንዲገቡ እያስገደደ መሆኑን አመልክተዋል።

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
🔊 #የጤናባለሙያዎችድምጽ

🔴
የጸጥታ አካላት ሆስፒታል ድረስ በመምጣት ድብደባ ፈጽመዋል፣ ዘጠኝ ሠራተኞችና የማኔጅመንት አባላትን አስረዋል ” - የሆስፒታሉ ሠራተኞች

➡️ “ እነርሱ ጋ ብቻ አይደለም ያልተከፈለው፤ ከ2000 በላይ ሠራተኞች እንደ ዞን ያልተከፈላቸው አሉ ”  - የጌዴኦ ዞን ጤና መምሪያ

በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ከተማ፣ የይርጋጨፌ ሆስፒታል ጤና ባለሙያዎችና የአስተዳደር ባለሙያዎች “ በጸጥታ አካላት ድብደባና እስራት ተፈጽሞባቸዋል ” ሲሉ ሠራተኞቱ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናገሩ።

ተፈጽሟል ስላሉት እስራትና ድብደባ ምክንያት ምን እንደሆነ ሲገልጹ፣ እንደ ሀገር የተደረገው የደመወዝ ጭማሪ ክፍያ ባለመፈጸሙ የሥራ ማቆም አድማ መደረጉን ተከትሎ መሆኑን ሠራተኞቹ አስረድተዋል።

የአራት ወራት የደመወዝ ጭማሪ ክፍያ ከ150 በላይ ለሚሆኑ የሆስፒታሉ ሠራተኞች አለመፈጸሙን፣ እስከ የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ/ም እንዲፈጸምላቸውና እስከተጠቀሰው ጊዜ ድረስ ካልተፈጸመላቸው ሥራ የማቆም አድማ ለማድረግ እንደሚገደዱ በደብዳቤ ጭምር ማሳወቃቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም ክፍያው ባለመፈጸሙ የሥራ ማቆም አድማ እንዳደረጉ፣ የተወሰኑት ሥራ ማቆም አድማ ያላደረጉ ሰራተኞች ቢሮ ባሉበት “ አድማ አስመትታችኋል ” በሚል እስራትና ድብደባ እንደተፈጸመባቸው በመግለጽ አማረዋል።

በዚህም፣ “የካቲት 10 እና 11 ቀን 2017 ዓ/ም ሥራ አልገባንም። በቀን 12/2017 ዓ/ም ደግሞ ሙሉ ፓትሮል ፓሊስ መጥቶ በሥራ ላይ የነበሩ የማኔጅመንት አባላትን ይዘው ወጡ ” በማለት ተናግረዋል።

አክለው፣ “ ከየቤቱ ያሉት ሠራተኞችም መረጃው ደርሷቸው ‘ካሰራችሁ ሁላችንንም እሰሩን የሁላችንም ጉዳይ ነው’ ብለው እስሩ ከተፈጸመበት ፓሊስ ጣቢያ ድረስ ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተዋል ” ሲሉ ሁነቱን አስረድተዋል።

የታሰሩት ምን ያክል ግለሰቦች ናቸው? ስንል የጠየቅናቸው ሠራተኞቹ በሰጡት ምላሽ፣ “የታሰሩት የሆስፓታሉ ሠራተኞችና የማኔጅመንት አባላት ናቸው፡፡ የጸጥታ አካላት ሆስፒታል ድረስ በመምጣት ድብደባ ፈጽመዋል፣ 9 ሠራተኞችና የማኔጅመንት አባላትን አስረዋል ” ብለዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ የሠራተኞቹን ቅሬታ በመያዝ፣ ድርጊቱ ለምን እንደተፈጸመ የጌዴኦ ዞን ጤና መምሪያ ቢሮን ምላሽ የጠየቀ ሲሆን፣ እስራቱ መፈጸሙን እና ደመወዙ አለመከፈሉን አምኖ ምላሽ ያለውን ሰጥቷል።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ አንዱዓለም ማሞ በዝርዝር ምን መለሱ ?

“ ባለሙያዎቹ የካቲት 7 መጥተው ነበር። ከኛ ጋ ውይይት አድርገዋል፡፡ ውይይት ካደረግን በኋላ ፕሮሰስ እያደረግን ለማክሰኞ ጠዋት ክልል ቀጠሮ እንደነበረ ገልጸንላቸው ነበር፡፡ ማክሰኞ ሂደን ዘጠኝ ሰዓት ላይ ምላሽ ታገኛላችሁ ብለናቸው ነበር፡፡

እነሱ ጋ ብቻ አይደለም ክፍያው ያልተከፈለው ከ2000 በላይ ሰራተኞች እንደ ዞን ያልተከፈላቸው አሉ፡፡ እንደ ዞንም ሶስት ሆስፒታል ላይ ነው ክፍያው ያልተከፈለው፡፡ የተለያዩ የጤና ባለሙያዎችም በወረዳ ደረጃ ያልተከፈላቸው አሉ፡፡

በሦስቱ ሆስፒታሎች ነው ያልተፈጸመው። ግን ሁለቱ ሆስፒታሎች የስራ ማቆም አድማ አላደረጉም፡፡ እነርሱ ግን ለማክሰኞ ቀጥረናቸው እያለ ቀጠሮውን አንቀበልም ብለው ሙያዊ ሥነ ምግባር በማይፈቅድ መንገድ ስራ የማመጽ ነገር አድርገው ነበር።

ግን የተወሰኑ ልጆች ደግሞ ስራ ገበታ ላይ ተገኝተው ነበር፡፡ ስለዚህ ኦሬዲ ድስከስ አድርገን ጉዳዩን ፈተን ልጆቹ ስራ ጀምረዋል አሁን፡፡ ስራ ላይ ናቸው ሁሉም ” ብለዋል።

ታሰሩ የተባሉት የሆስፒታሉ ባልደረቦች ሳይፈቱ እንዴት ሁሉም ስራ ላይ ሊገኙ እንደቻሉ ምላሽ የጠይቅናቸው ኃላፊው፣ “እነርሱ ያልተገባ አካሄድ የሄዱ አሉ፡፡ ከስነ ስርዓት ውጭ ያልተፈቀደ ሰልፍ የወጡበት ሂደትም አለ፡፡ እንግዲህ ከእስር እንዲወጡ እየተሰራ ያለበት ሂደት አለ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ሠራተኞቹ ቅሬታ ያቀረቡት የአራት ወራት ገደማ ደመወዝ አለመጨመሩን ተከትሎ ነውና የመብት ጥያቄ በመቅረቡ እስርና ድብደባ መፈጸም አግባብ ነው? ሲል ቲክቫህ ኢትዮጵያ ተጨማሪ ጥያቄ አቅርቧል።

አቶ አንዷለም በሰጡት ማብራሪያ፣ “ሠራተኞቹና ባለሙያዎቹ፣ ‘የፈጸምናቸው ድርጊቶች ትክክል አይደሉም ህዝቡን በድለናል ብለው’ ይቅርታ ጠይቀው ወደ ስራ ገብተዋል፡፡ ከአጠቃላይ ሰራተኞች ውይይት ተደርጎ ጤናማ ስራ ጀምረዋል አሁን” ሲሉ አስተባብለዋል።

ይቅርታ የጠየቁት ማን ናቸው? ሰራተኞቹ ወይስ አሳሪዎቹ? ስንል ላቀረብነው ጥያቄም  ኃላፊው፣ “ሰራተኞቹ ” ሲል የመለሰ ሲሆን፣ ታስረው እያለ እንዴት ይቅርታ ይጠይቃሉ? ሲል ቲክቫህ ኢትዮጵያ በድጋሚ ጥያቄ አቅርቧል።

እሳቸውም፣ “ሙያዊ ክብር በጣሰ መልኩ ሰልፍ የወጡትም ይቅርታ እየጠየቁ ነው ያሉት አሁን፡፡ ‘እነርሱ ናቸው ጥፋተኛ’ በሚል ልከውልናል ቤተሰቦቻቸው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የተወሰኑት ሠራተኞች የስራ ማቆም አድማ አድርገው ነበር፤ በአንጻሩ ደግሞ የተወሰኑት ደግሞ ስራ ላይ ተገኝተው ነበር፤ ነገርግን ‘ሌሎቹን አሳምጻችኋል’ በሚል ስራ የገቡትም ናቸው የታሰሩት። ሥራ ላይ እያሉ ታስረው ሳለ “ይቅርታ ጠይቀዋል” መባሉ ምን ማለት እንደሆም በድጋሚ ምላሽ ጠይቀናል።

አቶ አንዷለም በምላሻቸው፣ “ነገሩ እንግዲህ እንደዚሁ ነው። አሁን ውይይት ላይ ነን፡፡ እነርሱ የሰሩት ጥፋት ስለነበረ ነው የተጠየቁት። አሁን ይቅርታ ጠይቀው ውይይት ላይ ነን ችግሩን ለመፍታት” ነው ያሉት፡፡

እንዳጠቃላይ ችግሩን ለመፍታትስ ምን እየተሰራ ነው? ስንል ላቀረብነው ጥያቄም፣ “አሁን በጀቱ እውቅና አግኝቷል፡፡ ለሰራተኞች የጸደቀላቸው በጀት እጃችን ላይ ገብቷል፡፡ የክፍያ ሂደት ለማመቻቸት ጥረት እየተደረገ ነው” ብለዋል።

“ከክልል ፋይናንስ ገንዘብ እንድለቀቅ ሂደት ላይ እንደሆነና ያው ከዚያ እንደተለቀቀ ክፍያ እንደሚከፈል ተግባቦት ላይ ተደርሷል” ሲሉም አክለዋል፡፡

(ጉዳዩን እስከመጨረሻ የምንከታተለው ይሆናል)

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
የአደጋ_ደህንነት_ደንብ_ቁ_132_2014_የጸደቀ_250222_210150.pdf
327.8 KB
“ ማንኛውም ሰው በተቋሙ ውስጥ አስፈላጊ የአደጋ ደኅንነት መስፈርቶች ካላሟላ ከ10 ሺሕ ያላነሰ ከ100 ሺሕ ያልበለጠ ቅጣት ይጣልበታል ” - ኮሚሽኑ

የአደጋ ደኅንነት መስፈርቶችን ባላሟሉ አካላት የገንዘብና የሥራ ፈቃድን እስከማሳገድ ቅጣትን የሚደነግግ ደንብ ማውጣቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና ስጋት ሥራ አመራር አስታወቀ።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ የተመለከተው ደንቡ፣ “ማንኛውም ሰው በተቋሙ አስፈላጊ የአደጋ ደኅንነት መስፈርቶች ሳያሟላ የቀረ እንደሆነ እንደ ደረጃው ከ10 ሺሕ ያላነሰና ከ100 ሺሕ ያልበለጠ የገንዘብ ቅጣት ይጣልበታል” ይላል።

በኮሚሽኑ ደንብ መሠረት፦

ደንቡ፣ የህንፃዎችና የግንባታዎች ዲዛይን፣ ስለህንፃ፣ ግንባታና የግንባታ ሂደት መሟላት ያለባቸው የአደጋ ስጋት ደኅንነት መስፈርቶችንና የህንፃ አጠቃቀምን የተመለከቱ ግዴታዎችን አካቶ ይዟል።

የህንፃዎች ዲዛይን የሌሎች ሰዎችን ንብረቶች ለአደጋ በሚያጋልጥ መልኩ መሆን እንደሌለባቸው፣ በዲዛይኑ የእሳትና ሌሎች አደጋዎችን መከላከያና መቆጣጠሪያ መስፈርቶች መሟላት እንዳለባቸውም ደንቡ ያትታል።

ነባር ህንፃዎች ጥገና ወይም ለውጥ በሚደረግባቸው ጊዜ አደጋን ለመቆጣጠር/ለመከላከል የተገጠሙ ሲስተሞች ስለመሟላታቸው ፍተሻ ተደርጎ የአደጋ ደኅንነት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት መውሰድ ግዴታ መሆኑ ተመልክቷል።

በግንባታ ሂደት ያለ ህንፃ ሲጠናቀቅ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ለሚያዙ ክፍሎች አስፈላጊ የደኅንነት ተግባራት መሟላታቸው ካልተረጋገጠ ለተጠቃሚዎች መተላለፍ እንደማይችልም በድንጋጌው ተጠቅሷል።

ህንፃ ተከራዮች አደጋን አስቀድሞ ለመከላከል ወይም ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የአደጋ ደኀንነት መስፈርቶችን እንዲያሟሉ፣ የአደጋ ደኅንነት መስፈርቶችን ያላሟላ ነባር ህንፃ ባለቤት ለማሟላት የሚጠበቅበትን የማድረግ ግዴታ እንዳለበት በደንቡ ተገልጿል።

“ማንኛውም የጅምር ህንፃ ተጠቃሚ ከሚመለከተው አካል የመጠቀሚያ ፈቃድ መያዝ ይኖርበታል”ም ብሏል ደንቡ።

በተጨማሪም፣ አደገኛ ንጥረ ነገሮች የሚያከማቹ የሚያጎጉዙ፣ የሚጠቀሙ የደኀንነት የደኅንነት ብቃት ማረጋገጫ ሊኖራቸው እንደሚገባ፣ ኮሚሽኑ የተከማቹ አደገኛ ንጥረ ነገሮችን እንደሚያስወግድ አትቷል።

እንዲሁም የተከለከሉ ድርጊቶችን ዝርዝር ያስቀመጠው ደንቡ የንግድ/የሥራ ፈቃድ እስከማሳገድ የሚደርስ እርምጃ እንደሚያስወስድ ገልጾ፣ እርምጃ አወሳሰድና አስተዳደራዊ ቅጣት ዝርዝር ድንጋጌዎችን ደንቡ አስቀምጧል።

ኮሚሽኑ ይህንኑ ደንብና ለማህበረሰቡ ሊቀርብ ስለሚገባ ግንዛቤ በተመለከተ ከሚዲያ ተቋማት የምክክር መድረክ ትላንት በሳሬም ሆቴል ያካሄደ ሲሆን፣ ተጨማሪ ይኖረናል። 

(ሙሉ ድንጋጌ የያዘው ደንቡ ከላይ ተያይዟል)

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
#Update " ከ3,000 ወጣቶች ወደ 130 የሚሆኑት ወጡ ተብሎ ዝም የሚባል ከሆነ ለቀሪዎቹ አደጋ ነው " - የወላጆች ኮሚቴ ሰርተው ለመለወጥ በሚል ከኢትዮጵያ የተሰደዱ ዜጎች በማይናማር በአጋቾች የከፋ ስቃይ እያሳለፉ በመሆኑ መንግስት ከስቃይ እንዲታደጋቸው በተደጋጋሚ መጠየቁ አይዘነጋም።  የወላጆች ኮሚቴ፣ ኢትዮጵያዊያኑ በታገቱበት የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ አጋቾች ልጆቹን ዶላር ማጭበርበር…
#Update

🔴 “ መንግስት እንዲመጡ ስላላደረገ ከእገታው የወጡት ኢትዮጵያዊያንም በፓሊስ ተመልሰው እየተወሰዱ ነው። እስካሁን ሰባት ልጆች ተወስደዋል ” - ቤተሰብ

🔵
እኛ ዜጎች አይደለንም እንዴ? መንግስት ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ትዕዛዝ መስጠት አይችልም? ” - ኢትዮጵያዊ በታይላንድ

➡️ “ ልጆቻችን በረሃብ ሊያልቁብን ነው ” - የወላጆች ኮሚቴ

ሰርተው ለመለወጥ ሲሉ ተታለው ወደ ታይላንድ የተሰደዱና በታጣቂዎች በማይናማር ታግተው ቆይተው የወጡና አሁንም በእገታ ያሉ ኢትዮጵያዊያን መንግስት እንዲደርስላቸው በተደጋጋሚ መጠየቁ ይታወሳል።

በሺዎች ከሚቆጠሩት ኢትዮጵያዊያን ታጋቾች ውስጥ 13ዐ የሚሆኑት ከሳምንታት በፊት ከእገታ እንደተለቀቁ፣ ሌሎች በርካቶች ደግሞ ገና ከእገታው እንዳልወጡ፣ የወጡትም ሆኑ ያልወጡት የመንግስትን ድጋፍ እየተጠባበቁ መሆኑን መረጃ አድርሰናችሁ ነበር።

በታይላንድ ያሉ ኢትዮጵያዊያኑ አሁንስ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ምን አሉ ?

“ ከመግደል ያላነሰ ድብድባ ነው የሚካሄደውኮ። እኛ ዜጎች አይደለንም እንዴ? መንግስት ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ትዕዛዝ መስጠት አይችልም ?

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ታይላንድ በረራ እንዳለው እያየን ነው። እሺ ገበያውም አይዘጋበት ቢያንስ ሰው ይዞ ወደ ታይላንድ መጥቶ ሲመለስ የተወሰኑ ሰዎችን እየቀላቀለ ቢመልሰን ማቃለል አይችልም ? 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኛ አይደለም እንዴ ? ለሥራ ብለን ነው የመጣነዎኮ ስለተቸገርን ገንዘብ ለማግኘት። ገንዘብ ይዘን ደግሞ ወደ ሀገራችን ለመመለስ። 

‘መንግስት አላችሁ?’ ተብለን እስከምንጠየቅ መድረሳችን በጣም ያሳፍራል። የኢትዮጵያ መንግስት ለሌላ አገር ‘ገንዘብ ረዳሁ’ ብሎ ከሚያወራ እዚህ ያሉትን ዜጓቹን አያስወጣም እንዴ ? 

እኛስ መቼም ምግብ ባይቀርብልም ከነበርንበት ሁኔታ አንጻር ምንም አይመስለንም። ትኩረት የሚሹት በማይናማር ከእገታ ያልወጡት እኛ ባለን መረጃ ብቻ እንኳ ከ400 በላይ ለሆኑ ኢትዮጵያዊያን ነው። እነርሱ የሚወጡት ደግሞ እኛ ቦታውን ስንለቅላቸው ነው።

እኛ ማይናማር ቦርደር ላይ ነው ያለነው። ሞኤ የሚባል ወንዝ እንደተሻገን። በጣም ሐበሻዎች አሉ። ከአንድ ካምፓኒ ብቻ እስከ 500 የሚደርሱ ሐበሻዎች አሉ።

አብዛኛው ኢትዮጵያ ያለበት አንዱ ካምፓኒ ‘ወደ ሌላ ቦታ እንስዳችኋለሁ’ እያለን ነው። ሌላ ቦታ የሚወስደን ሁሉንም ነገሮች ቁጥጥሩ ለማድረግ ነው። አሁን ያለንበት ቦታ ላይ ደኀንነታችን የተጠበቀ ነው። 

ማይናማር ግን ብዙ ሰው እየተጎዳ፣ እየተሰቃዬ ያለበት ፎረይን ፓሊሶች የሌሉበት አካባቢ ነው። ያለንበትን ካምፓኒ አቋርጠን ለመውጣት 2,500 ዶላር ይከፈላል። ያለንበት ግቢ እስከ 25 ካምፓኒዎች አሉ። ወደ ሌላ ግቢ ላለመሄድ ነው ጥረት እያደረግን ያለነው።

ሐበሾችን እየጠበቅን ነው ገና ከእገታ ያልወጡ ስላሉ። አመት ድረስ የቆዩ አሉ። በራሳችን ፈቃድ ስለማያስወጡን። 

እስካሁን ወደ ኢትዮጵያ ያልመጣንበት ዋነኛው ምክንያት ሙሉ ወጪ መሸፈን ስላማይችል ነው። 

ምክንያቱም ወደ ኢትዮጵያ መንግስት ደብዳቤ ልከው ከኢትዮጵያ መንግስት ምንም አይነት ምላሽ እንዳላገኙ ነው መረጃ የሰጡን። የታይላንድ መንግስት ለኢትዮጵያ መንግስት ደብዳቤ ልኳል። ግን እስከ ሳምንት ምላሽ አልተሰጠም።

ካለንበት ካምፕ ወጥተን ወደ ታይላንድ/ሜኢሶት ኤርፓርት ነው መሄድ ያለብን። ከታይላንድ መንግስት ጋር በመነጋገር ወንዝ ያሻግሩናል። ፓስፓርት የሌለው አንድ ወር መቆየት እንደሚችል ነው የተነገረው። 

የተጎዱ ሀበሿች፣ ጀርባቸው ላይ ለምጥ ያለ፣ የታመሙ፣ የተደበደቡ በሙሉ ካምፕ ነው ያሉት። እኛን ኢትዮጵያዊያንን ብቻ ነው ያልጠየቁን እንጂ ህንዶችን፣ ቻይናዎችን ‘አለንላችሁ’ የሚሉ አሉ። 

ምን እያደረጉ እንደሆነ የምናውቀው ነገር የለም። የምናውቀው ዘገባ እያደረጉና ዜግነታችንን ለይተው ብዙ ነገር እየጠየቁ እንደሆነ ነው። 

የኢትዮጵያ ዜጎች ብቻ ናቸው የቀሩት። ከኢትዮጵያ መንግስት ምላሽ ስላላገኙ። ምላሽ ቢያገኙ ይወጡ ነበር የሚቆዩበት ምክንያት የለም። ለኛም ስጋት የሆነው እነርሱ ባለመሄዳቸው የተነሳ ምናልባት የታይላንድ መንግስት ላይቀበለን ይችላል ” ሲሉ ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያዊያኑ ቤተሰቦችስ በሰጡን ቃል ምን አሉ ?

“ ከእገታው ያልወጡ ኢትዮጵያዋያን ስቃይ ላይ ናቸው። ከእገታ ከወጡት 261 ዜጎች 138 ኢትዮጵያዊያ ናቸው። ከማይናማር ተነስተው ታክ በሚባል ካምፕ ነው ያሉት፤ ከቦርደሩ 82፣ ለባንኮክ 377 ኪሎ ሜትር ርቀት።

ቦታው አሁን ለደኀንነታቸው አስተማማኝ እየሆነ አይደለም። ምክንያቱም ከወጡት 261 የ18 ሀገራት ዜጎች በስምንት ቀናት ሁሉም ወደ ሀገራቸው ሂደዋል። የቀሩት የኢትዮጵያ ዜጎች ብቻ ናቸው።

ከእገታው እንደወጡ ኢንተርቪው ተደገው ነበር በዛው አካባቢው አካላት፣ የደረሰባቸውን ስቃይ ተናግረው ነበር። ቃለመጠይቁን የሰሙ የታይላንድ ፓሊሶችም መልሰው ወስደዋቸዋል። መንግስት እንዲመጡ ስላላደረገ የወጡት ኢትዮጵያዊንም በፓሊስ ተመልሰው እየተወሰዱ ነው። እስካሁን ሰባት ልጆች ተወስደዋል። የተመለሰ የለም።

የሌሎቹ ሀገሪት ዜጎችም ኢንተርቪው ተደርገው የነበር፤ ነገር ግን ኤምባሲዎች ሂደው በቀናት ውስጥ ነው የወሰዷቸው። 138ቱ ኢትዮጵያዊን ከእገታው ቢወጡም ወደ ኢትዮጵያ ስላልወጡ አደጋ ላይ ናቸው።

በታይላንድ ካምፕ ላይ ያሉት 138፣ በሌላ ጉዳይ ምክንያት በታይላንድ ፓሊስ ቁጥጥር ስር የሚገኙ፣ ገና ቦርደር ላይ እየጠበበቁ ያሉ 100 በአጠቃላይ 259 ኢትዮጵያዊያን ስም ዝርዝራቸው እንደተላከለት ውጪ ጉዳይ ነግሮናል።

በስም ዝርዝራቸው መሠረት መረጃዎችን እያደራጀ እንደሆነ ቢገልጽልንም እስካሁን ድረስ ግን ምንም አይነት ተጨባጭ የሆነ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተሰራ ነገር የለም።

የወጡት ኢትዮጵያዊያን ከኢትዮጵያ መንግስት የሚጠብቁት ምን እንደሆነ፥ የአገልግሎት ጊዜው ያለቀ ፓርፓርት ያላቸው ልጆች ስላሉ ማንንነታቸውን የሚገልጽ መታወቂያ ወደ ታይላንድ መንግስት እንዲልክላቸው፣ የበረራ ትኬቶች እንዲስተካክልላቸው ነው” ብለዋል።

የወላጆች ኮሚቴ በበኩሉ ፦

“ የታይላንድ መንግስት ‘ዜጎቻችሁን ውሰዱ’ ካለ በኋላ ብዙ ሀገራት ልጆቻቸውን አስወጥተዋል። የኢትዮጵያ ልጆች ግን እየተሰቃዩ ነው ያሉት።

የተወሰኑት አምልጠው ሲወጡ ተከትለው ለወጣት የምከሩ ኢትዮጵያዊያን ማይናማር በወታደሮች ካምፕ ታጉረዋል። ከእገታ የወጡት ወደ ሀገቸው ስላልመጡ ሌሎች ያልወጡት ታጋቾችም እየተሰቃዩ ነው።

አሁንም ወታደራዊ ካምፕ ያሉ ኢትዮጵያዊያኑ ብቻ ናቸው። ምግብም እየተሰጣቸው አይደለም። ልጆቻችን በረሃብ ሊያልቁብን ነው። ልጆቹ ያልወጡበት ምክንያት ያገራችን መንግስት ባለመቀበሉ ብቻ ነው” ሲል ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጿል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ፣ ለምን ከእገታ የማጡት ኢትዮጵያዊንን በአፋጣኝ ማምጣትና የታገቱትን ወገኖች ለማስለቀቅ ለምን እንዳልተቻለ ለውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥያቄ ቢያቀርብም እስካሁን ምላሽ አላገኘም።

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
“ አንዳንድ ጊዜ አደጋዎች ከተስፋፉ በኋላ የመደወል ሁኔታ አለ። በ939 ፈጥኖ መደወልም ያስፈልጋል ቶሎ ደርሰን እንድንቆጣጠር ” - ኮሚሽኑ

ዛሬ አዲስ አበባ ፤ ኮልፌ ቀራኒዮ፣ ወረዳ 2 በተለምዶ ካሬ ቆሬ ብቄላ መናፈሻ አካባቢ ተነስቶ የነበረው የእሳት አደጋ በሰው ላይ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የእሳትና አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጿል።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ንጋቱ ማሞ በሰጡን ቃል፣ “ እሳቱ ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ስር ውሏል ” ብለዋል።

“ የፍራሽ መስሪያ የሚሆኑ (ቁርጥራጭ ጨርቅ) የመሳሰሉ ግብዓቶች መጋዘን ላይ ነው የእሳት አደጋው ያጋጠመው ” ያሉት አቶ ንጋቱ፣ የኮሚሽኑ ሰራተኞች፣ ህብረተሰቡ ባደረጉት ርብርብ እሳቱ ወደ መስጊድና መኖሪያ ቤት ሳይዛመት መቆጣጠር መቻሉን አስረድተዋል።

“ በእሳት አደጋው ሰው ላይ ጉዳት አልደሰም። የቀረው መረጃ በኢኮኖሚ ላይ የደረሰው ጉዳትና የአደጋ መንስኤ ነው። እሱን ከፓሊሶች ጋር ሆነን እያጣራን ነው ” ሲሉ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል። 

የእሳት አደጋ እየተደጋገመ ያለበት ሁኔታ እየተስተዋለ ነው፤ ማህበረሰቡ ምን አይነት ጥንቃቄ ማድረግ አለበት ? ስንል ሳቀረብንላቸው ጥያቄ አቶ ንጋቱ፣ “ ትክክል ነው እሳት አደጋ የተደጋገመመበት ሁኔታ አለ። አሁን ያለንበት ወቅት ነፋሻማና ደረቅ አየር ነው ” የሚል ምላሽ ስጥተዋል።

“ እሳት እንዲከሰት ከሚያደርጉ ሦስት መሰረታዊ ጉዳዮች ውስጥ ሁለቱን አሁን ካለው የአየር ፀባይ እናገኛለንና መዘናጋትና ቸልተኝነት ዋጋ የሚያስከፍልበት ሂደት ስላለ ህብረተሰቡ በመኖሪያ፣ በስራ አካባቢ እሳትና የኤለክትሪክ ኃይል ምንጮችን ሲጠቀም ከወትሮው በተለዬ ሁኔታ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ” ሲሉ አክለዋል።

“ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ያድርግ። ከዚህ አልፎ ለሚያጋጥም አደጋ፥ አንዳንድ ጊዜ አደጋዎች ከተስፋፉ በኋላ የመደወል ሁኔታ አለ። በ939ኝን ፈጥኖ መደወልም ያስፈልጋል ቶሎ ደርሰን እንድንቆጣጠር” ሲሉ አሳስበዋል።

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
" በአደራ የሰበሰብነውን ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ለተለያዩ አገር በቀል ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ለግሰናል " - ዳሽን ባንክ

ዳሽን ባንክ ዛሬ “ ሸሪክ ” የተሰኘውን ከወለድ ነፃ አገልግሎት የ7ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በዋና መስሪያ ቤቱ አክብሯል።

በዚህም ከደንበኞቹ በአደራ የሰበሰበውን ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ለተለያዩ አገር በቀል ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች መለገሱን አስታውቋል፡፡ 

በዛሬው ዕለትም ለ31 ሀገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ መደረጉ ነው የተገለጸው።

በከወለድ ነፃ አገልግሎት ብቻ ከ1 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ማፍራት መቻሉ የተገለጸ ሲሆን፣ የአገልግሎቱ ቺፍ ኦፊሰር አቶ መስፍን በዙ ባደረጉት ንግግር አመኔታቸውን ለሰጡ ደንበኞች ምስጋና አቅርበዋል።

የካቲት 26/2010 ዓ/ም በአንድ መስኮት የተጀመረው አገልግሎት አድጎ ከ80 በላይ ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ቅርንጫፎችና ከ800 በላይ በሆኑ ቅርንጫፎች በመስኮት ለደንበኞቹ የተሟላ የባንክ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።

በሱማሌ ክልል ለሚገኙ ሴት ስራ ፈጣሪዎች ከወለድ ነጻ በሆነ መንገድ 100 ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ብድር ማቅረቡን አስታውሷል።

" ሸሪክ " እ.ኤ.አ ህዳር 28/ 2023 በባህሬን ማናማ በተካሄደው 9ኛው የኢስላሚክ ሪቴል ባንክ ሽልማት ላይ “ጠንካራ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በኢትዮጵያ የሚሰጥ ባንክ” በሚል አይ ኤፍ ኤ ከተሰኘው ድርጅት ዕውቅና ማግኘቱ ተገልጿል።

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
🔊 #የጤናባለሙያዎችድምጽ 🔴 “ የጸጥታ አካላት ሆስፒታል ድረስ በመምጣት ድብደባ ፈጽመዋል፣ ዘጠኝ ሠራተኞችና የማኔጅመንት አባላትን አስረዋል ” - የሆስፒታሉ ሠራተኞች ➡️ “ እነርሱ ጋ ብቻ አይደለም ያልተከፈለው፤ ከ2000 በላይ ሠራተኞች እንደ ዞን ያልተከፈላቸው አሉ ”  - የጌዴኦ ዞን ጤና መምሪያ በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ከተማ፣ የይርጋጨፌ ሆስፒታል ጤና ባለሙያዎችና የአስተዳደር ባለሙያዎች “ በጸጥታ…
#Update

🔴 “ ወደ አራት ጤና ባለሙያዎች ገና አልተፈቱም። የጠየቁት መብታቸውን ስለሆነ ሊፈቱ ይገባል ” - ቤተሰቦች

➡️ “ ሰልፍ ላይ ስለተገኙ ብቻ ነው የተያዙት ” - ጤና ባለሙያ


የአራት ወራት አዲሱ ደወመዝ ክፍያ ስላልተፈጸመላቸው የሥራ ማቆም አድማ በመምታታቸው ከታሰሩት የይርጋጨፌ ሆስፒታል ጤና ባለሙያዎች መካከል አራቱ እንዳልተፈቱ ቤተሰቦቻቸውና የጤና ባለሙያዎች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።

መጀመሪያ የታሰሩት ዘጠኝ እንደነበሩ ሠራተኞቹ ከቀናት በፊት ለቲክቫህ ኢትዮጵያ መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ እስራቱ ቀጥሎ በአጠቃላይ 12 ሰዎች ታስረው እንደነበርና አራቱ እንዳልተፈቱ ነግረውናል።

የታሳሪ ቤተሰቦችና ጤና ባለሙያዎች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ምን አሉ ?

አንድ ጤና ባለሙያ በሰጡን ቃል፤ “ የተፈቱና ሌሎቹም በሥራ ገበታ ላይ ናቸው። የነዚህ የአራቱ አለመፈታት ግን እስካሁን ምስጢር ሆኖብናል። ሰልፍ ላይ ስለተገኙ ብቻ ነው የታሰሩት ” ሲሉ ተናግረዋል።

የታሳሪ ቤተሰቦች በበኩላቸው “ አራት ጤና ባለሙያዎች ገና አልተፈቱም። የጠየቁት መብታቸውን ስለሆነ ሊፈቱ ይገባል ” ብለዋል።

“ ጥያቄው የሆስፒታሉ አካላት ሁሉ ነው። የፓለቲካ ጉዳይ የሌለበት የደመወዝ ጥያቄም ነው። ከደመወዝ ይከፈለን ውጪ ያነሱት ጥያቄ የለሞ ” ሲሉም ሞግተዋል።

አንዲት የታሳሪ ቤተሰብ በሰጡን ቃል፣ ባለቤታቸው ከታሰሩ ቀናት እንዳስቆጠሩ፣ እስካሁንም እንዳልተፈቱ፣ ያሉበትን ሁኔታም እንደማያውቁ ገልጸዋል።

ሌላኛው የታሳሪዋ የቅርብ ሰው የ10 ወር ጨቅላ ህፃን ያላት ጤና ባለሙያ እንደታሰረች ገልጸው፣ በዋስ እንደትለቀቅ እንኳ ቢሞከር ፈቃደኛ አካል አለመኖሩን ጠቁመዋል።

“ አጥቢ ከመሆኗ አንፃር ቀነ ገደብ ተጠይቆ ነበር። ፍርድ ቤት ዋስትና እንዲሰጣት ውሳኔ ቢያስተላልፍም እንዳትወጣ በፓሊስ ተከልክላለች ” ሲሉ ነው የወቀሱት።

የታሳሪ ቤተሰቦች፣ የታሰሩት የጤና ባለሙያዎች እንደሆኑ፣ ብዙ የህክምና ተገልጋዮች መጉላላታቸውም ከግምት ሊገባ እንደሚገባ አሳስበው፣ በፍጥነት እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

የታሰሩት ለምን እንዳልተፈቱ ምላሽ ለማግኘት የጸጥታ አካላትን ለማካተት የተደረገው መከራ ስልክ ለማንሳት ፈቃደኞች ባለሆናቸው ለጊዜው አልተሳካም።

የጌዴኦ ዞን ጤና መምሪያ ከዚህ ቀደም  ጠይቀነው፣ በሌሎች ሆስፒታሎችም ጭምር ከ2000 በላይ ሠራተኞች ክፍያው እንዳልተፈጸመላቸው፣ የታሰሩትን ለማስፈታትም እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ነበር።

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
" ከየካቲት 24 በኋላ የፋይዳ መታወቂያ የሌለው ደንበኛ የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር ትኬት መቁረጥ አይችልም " - የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር አክስዮን ማህበር

የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር መንገድ አክስዮን ማህበር ለመንገደኞች የጉዞ ትኬት የሚያገኙበትን መንገድ ከሰኞ የካቲት 17/2017 ዓ/ም ጀምሮ  ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ ማድረጉን ገልጿል።

ከሁለት ቀን በፊት የተጀመረውን በኦንላይን ትኬት የመቁረጥ ሂደት አገልግሎቱን ለማግኘት የፋይዳ መታወቂያ ግዴታ መደረጉን የኢትዮጵያ ጅቡቲ የባቡር መንገድ አክስዮን ማህበር የኮምዩኒኬሽን ባለሞያ የሆኑት ወ/ሮ እስራኤል ወልደ መስቀል ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

ወ/ሮ እስራኤል " ማስታወቂያዎችን ስንሰራ የቆየን በመሆኑ የፋይዳ መታወቂያ ግዴታ ነው ነገር ግን ይሄንን ሳምንት ልዩ በሆነ መንገድ እና ሰውም የአጠቃቀም ጉድለት ስላለ የጉዞ ትኬት እየቆረጥን እንገኛለን ከሚቀጥለው ሳምንት ሰኞ በኃላ ግን ያለ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የባቡሩን ትኬት ማግኘት አይቻልም " ብለዋል።

ክፍያው የሚፈጸመው በቴሌ ብር ሲሆን አገልግሎቱን ለማግኘት ለሃገር ውስጥ ተጠቃሚዎች የፋይዳ የምዝገባ ቁጥራቸውን ኢትዮጵያዊ ላልሆኑ ተጠቃሚዎች ደግሞ ፓስፖርታቸውን በመጠቀም ትኬት ማግኘት እንደሚችሉ አሳውቀዋል።

ባለሞያዋ በትኬት ዋጋ ላይ ምንም አይነት ጭማሪ አለመኖሩን አንስተው በነባሩ ዋጋ ዲጂታላይዝ ብቻ መደረጉን ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ ፉሪ የሚገኙ የትኬት ሽያጭ ቢሮዎች አሰራሩ ዲጂታላይዝ ስለሆነ የመንገደኞችን የአገልግሎት ትኬት የመቁረጥ ስራ እንደማይሰሩ ወ/ሮ እስራኤል ገልጸዋል።

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
“ የአንድ አዞ ቆዳ አንድ ሴንቲሜትር 5 ዶላር ነው የሚሸጠው ” - የጋሞ ልማት ማኀበር

በተለይ የውጪ አገር የገበያ ትስስር ባለመኖሩ ኢትዮጵያ ከአዞ ሽያጭ እስከ 60 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ እያጣች መሆኑን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባምንጭ የጋሞ ልማት ማኀበር ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገለጸ።

ከሦስት ዓመታት በፊት ትንሽ የአዞ ስጋና ቆዳ ለውጪ አገራት ይሸጥ እንደነበር፣ ከዚያ በኋላ በገበያ ትስስር ክፍተት ገቢው በመቀዛቀዙ እንደ አዲስ ለማንሰራራት እየተሰራ መሆኑን ማኀበሩ አስረድቷል።

ስለአዞ ሽያጭ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ማብራሪያ የጠየቃቸው የማህበሩ አርባምንጭ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት ዳኘ፣ “ ከ3 አመታት በፊት 10፣ 15 ነበር የሚሸጠው። ከ3000 እስከ 5000 አዞዎች ሲሸጡ የነበረው ከ10 ዓመት በፊት ነው። እየቀሰ መጥቷል ” ብለዋል።

የማኀበሩ ሥራ የአርባምንጭ አስኪያጅ አቶ ዲዊት ዳኘ ምን አሉ ?

“ የአዞ ቆዳ የሽያጭ ሂደቱ ተቀዛቅዞ ቆይቶ አሁን ሽያጭ አልተጀመረም። አሁን በማኀበሩ ተወስዶ እየተሰራ ነው። ቆዳቸው ለሽያጭ የደረሱ ከ2500  በላይ አዞዎች አሉን። እንዴት እንደሚቀጥል ከአገር ውስጥ ካምፓኒዎች ጋር እያወራን ነው።

አሁን ተነጋግረን የውል ሂደት ላይ ነው ያለነው እሱን ጨርሰን ሽያጩ ይካሄዳል ብለን እናስባለን። በፊት ሲሸጥ የነበረው ቆዳው ብቻ ነው። ግን የአዞ ስጋው፣ ጥርሱ፣ ይፈለጋል። ስጋው በሌሎች አገራት በጣም ይፈለጋል።

አሁን 4,000 የአዞ ጫጩቶችን ለመሰብሰብ እንቁላል ዝግጁ ሆኖ ነው ያለው። ከሦስት ወራት በኋላ ጫጩት ከተፈለፈለ በኋላ ከሀይቁ ወደ ማኀበር ይመጣሉ።

የአዞ ቆዳና ስጋ በጣም ዋጋው ውድ ነው። ስለዚህ ትክክለኛ ማርኬት ሊንኬጅ ተፈጥሮ ስርዓቱ ቢዘረጋ እንደ አገር ትልቅ ገቢ እናገኛለን። በተለይ በዘርፉ የሚሰሩ የውጪ አገር ካምፓኒዎችን እያነጋነርን ነው ” ብለዋል።

ከ2,500 በላይ አዞዎች ለሽያጭ ቢቀርቡ ምን ያክል ገቢ ማግኘት ይቻላል ? ስንል የጠየቅናቸው አቶ ዳዊት፣ የአንድ አዞ ቆዳ አንድ ሴንቲሜትር 5 ዶላር እንደሚሸጥ፣ የአንድ አዞ ቆዳ እስከ 45 ሴንቲሜትር እንደሚሆን፣ አንድ አዞ በትንሹ እስከ 22 ሺሕ ብር እንደሚሸጥ፣ በጠቅላላ ከ55 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ሊገኝ እንደሚችል አስረድተዋል።

በማኀበሩ ስንት ሠራተኞች አሉ ? የአዞ ስጋ ምግብነት ላይ ይውላል ወይ ? ለሚለው የቲክቫህ ኢትዮጵያ ጥያቄ አቶ ዳዊት፣ “ የአዞ ስጋ ይበላል። በኛ አልተለመደም። ግን የኛ ሰዎች የ40 ዓመት ልምድ አላቸው። ብራንቹ ተቋቁሞ 41 ዓመቱ ነው። ረጅም ልምድ ያላቸው ሰዎች አዞ የመመገብ ልምድ አላቸው ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

አቶ ዳዊትና አንድ የማኀበሩ አስጎብኝ በኢትዮጵያ ብዙ እንዳልተለመደ፣ ኬኒያን ጨምር በሌሎች አካባቢዎች አዞ ለምግብነት እንደሚውል ተናግረዋል።

አቶ ዳዊት፣ “ የአዞ ሬስቶራንት ለመክፈት ” እንዳሰቡ ገልጸው፣ “ ፈረንጆች ይመጣሉ እዚህ ይመገባሉ፤ ቀስ በቀስ የኛ ሰዎችም እያዩ እየተመገቡ ይሄዳሉ ” ነው ያሉት።

አክለው፣ በማኀበሩ ወደ 35 ገደማ ሠራተኞች እንዳሉ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ የገለጹ ሲሆን፣ የማኀበሩ አስጎብኝ በሰጡት ገለጻ ደግሞ፣ “60 በመቶ የሚሆኑት ሰራተኞች የአዞ ስጋ ይመገባሉ” ብለዋል።

አንድ አዞ ለሽያጭ ለመቅረብ ብቁ እስከሚሆን ድረስ 62 ኪሎ ግራም ስጋ እንደሚመገብ፣ አዞ የሚመገበው የአሳ፣ የአዞ ስጋ እንደሆነ፣ አሳማ ሌሎች የእንስሳት ዝርያዎች እንዳሉ፣ የህክምናና ሌሎችን ጨምሮ በአጠቃላይ ማኀበሩ በአመት እስከ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚደረግ ተመልክቷል።

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
#ፐርፐዝብላክ ° " ሥራ ላይ የነበሩ ሱቆችም የቤት ኪራይ መክፈል ስላልተቻለ ሊዘጉ ነው " - የፐርፐዝ ብላክ ባለአክሲዮኖች ° " በፍርድ ቤት የተያዘ ጉዳይ ስላለ ምንም  አይነት መግለጫ አንሰጥም " - ድርጅቱ የፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ ባለአክሲዮኖች፣ የድርጅቱ አካላት መታሰራቸውን ተከትሎ ድርጅቱ ላይ ባላቸው ሼር ላይ ሥጋትና ቅሬታ እንዳደረባቸው፣ ለቅሬታቸው አፋጣኝ ምላሽ  እንዲሰጣቸው በቲክቫህ…
“ ድርጅቱ ለኪራይ፣ ደመወዝና ለሌሎች ወጪዎች ክፍያ ባለመፈጸሙ ሠራተኛው ከፍተኛ ችግር ላይ ወድቋል ” - የፐርፐዝ ብላክ ባለአክሲዮኖች

ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ ሕብረት ባንክ ካለው ገንዘብ ውጪ በሌሎች ባንኮች ያለውን ገንዘብ እንዲያንቀሳቅስ ፍርድ ቤት ውሳኔ ቢሰጥም በዐቃቢ ህግ ይጎባኝ ውሳኔው መታገዱን የፍርድ ቤት ሰነድና ባለአክሲዮኖች አመለከቱ።

ሁነቱን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ያስረዱት ባለአክሲዮኖች የፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ አካውንት ለሰባት ወራት ተዘግቶ መቆየቱን፣ በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለደመወዝና ሥራ ማስኬጃ ክርክር ሲካሄድ ቆይቶ እንደነበር ገልጸዋል።

በክርክር ሂደቱም፣ ፍርድ ቤት ሕብረት ባንክ ከተቀመጠው ገንዘቡ ውጪ በሌሎች ባንኮች ያለው የፐርፐዝ ብላክ ገንዘብ እንዲንቀሳቀስ፣ ለማንቀሳቀስ አስተዳዳሪ እንዲሾም ወስኖ እንደነበር አስረድተዋል።

“ነገር ግን ዐቃቤ ሕግ ውሳኔውን በመቃወም ይግባኝ ጠይቆ የስር ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሳኔ አሳግዶታል” ብለዋል።

“ድርጅቱ ለኪራይ፣ ደመወዝና ለሌሎች ወጪዎች ክፍያ ባለመፈጸሙ ሠራተኛው ከፍተኛ ችግር ላይ ወድቋል” ያሉት ባለክሲዮኖቹ፣ “ድርጅቱ የሚፈርስ እንኳን ከሆነ አግባብ ባለው መንገድ መፍረስ ነበረበት እጅግ ከባድ ሁኔታ ተፈጥሯል” ሲሉ አማረዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ የተመለከተው ሰነድ፣ “መዝገቡ ከቀጠሮ በፊት የቀረበው ይግባኝ ባይ በቀን 10/6/2017 ዓ/ም በተፃፈ አቤቱታ ያቀረዝነው ይግባኝ ታይቶ የመጨረሻ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ የፌ/ከፍ/ፍርድ ቤት በወ/መ/ቁ 326384 የሰጠው ውሳኔ ታግዶ እንዲቆይ እንዲታዘዝልን በሚል ባቀረበው አቤቱታ ነው” ይላል።

አክሎም፣ ይግባኝ ቅሬታ ለመስማት ለ20/06/2017 ዓ/ም የተያዘው ቀጠሮ ተሰብሮ የእግድ አቤቱታውን በመመርመር ዝርዝር ትዕዛዝ መስጠቱን ያስረዳል።

የፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ አካውንቶች መዘጋታቸው፣ የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍስሃ እሸቱ (ዶ/ር) አገር መውጣታቸው አይዘነጋም።

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
“ የጤና መድን ክፍያ በሚል ማህበረሰቡ ከ3,000 ብር  በላይ በግዴታ እንዲከፍል እየተደረገ ነው ” - የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች

የጤና መድን ክፍያ በሚል ማህበረሰቡ ከ3,000 ብርና ከዚያ በላይ፣ ለኮሪደር ልማት ከ500 እስከ 20 ሺሕ ብር  በግዴታ እንዲከፍል እየተደረገ መሆኑን የባሕር ዳር ከተማ ነዋረዎች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናገሩ።

“ ከትንንሽ ምግብ ቤት ጀምሮ በማንኛውም የንግድ ሥራ የተሰማራ ቤተሰብ የሌለውንም ጨምሮ ነው እያስገደዱና የማይከፍለውን እያሸጉ ያሉት ” ሲሉ ገልጸዋል።

“ ከዚህ ቀደም ትዳር መስርቶ፣ ወልዶ የሚኖር ሰው አባል ሆኖ የአባልነት ክፍያ ነበር የሚከፍለው ለጤና መድን አሁን ግን ትዳር የሌላቸው በንግድ ሥራ የተሰማሩ ወጣቶችን ጭምር አባል ሳያደርጉ ብር ብቻ እያስከፈሉ ነው ” ብለዋል።

በሌላ በኩል፣ “ ለኮሪደር ልማት በሚል በማንኛውም ንግድ ሥራ የተሰማራ ሰው ተገዶ እንዲከፍል እየተደገ ነው ” ሲሉ ነዋሪዎቹ አማረዋል።

አክለውም ፦

“ ነዋሪውበኑሮ ውድነት እየተሰቃየ ነው ያለው። በአነስተኛ ንግድ የተሰማራው ነጋዴም ስራ ቆሞበታል። ምክንያቱም ተጠቃሚ የለም።

ህዝቡ ግብር ከፍሎ እንደገና ‘ለኮሪደር ልማት፣ ለጤና መድን’ ሲጨምርበት ከአቅም በላይ ሆኖበታል። ይሄ ነገር ከተጀመረ ቆይቷል። ግዳጁ አሁንም ተባብሶ ቀጥሏል። 

የማህበረሰቡም፣ ‘የኑሮ ውድነት ጫናው ቢኖርብንም በህግ አግባብ የተጣለብንን ግብር በሰዓቱ እየከፈልን ነው የምንሰራው። አሁን ላይ ስራ ተቀዛቅዟል። ተጨማሪ ክፍያ የመክፈል አቅም የለንም’ የሚል ቅሬታ አለው።

የኮሪደር ልማቱን ክፍያ በሚመለከት የከተማ አስተዳደሩ ከከፍተኛ ባለሀብቶች ጋር ውይይት አድርጎ ልማቱን እንደሚደግፉ ተስማምተዋል። ነገር ግን ዝቅተኛ ነጋዴዎች ተሳታፊ አልነበሩም። እነሱም ቢሆኑ ልማቱን ይደግፋሉ ነገር ግን ክፍያው አቅምን ያገናዘበ አይደለም።

በካሬታ ውሃና ሌሎች ሥራዎችን የማጓጓዝ ስራ ከሚሰሩ ልጆች ጀምሮ እስከ ቤት አከራይ ለኮሪደር ልማት መዋጮ እየተጠየቀ ነው። ዝቅተኛው 500 ብር ሲሆን፣ እስከ 20,000 ብር የተጠየቁ አሉ። 20 ሺሕ ብር አከራይ ብቻ ነው የሚከፍለው ” ሲሉ አማረዋል።

ነዋሪዎቹ ቅሬታውን ምላሽ እንዲሰጥበት የባሕርዳር ከተማ አስተዳደርን የጠቆሙ ሲሆን ምን ምላሽ እንዳላቸው የጠየቅናቸው  የከተማው ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው ቅሬታውን ከሰሙ በኋላ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ጤና መድን አገልግሎትን የጠየቀ ሲሆን፣ ምላሹ ሲገኝ የሚቀርብ ይሆናል።

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
#የአርሶአደሮችድምጽ🔈

🔴 “ ለሦስት ዓመታት ምንም የካሳ ክፍያ አልተከፈለንም፡፡ የምንመገበው አጥተን ለልመና ተዳርገናል” - አርሶ አደሮች

➡️ “ ክፍያዎቹን በተገቢው በሚፈለገው አግባብ እየከፈልን አይደለም ” - የአማራ ክልል መንገዶች
ቢሮ

በደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ ከቸና እስከ መካነ ኢየሱስ ከተማ ባለው የመንገድ ፕሮጀክት መሬት የተወሰደባቸው ወደ 40  አርሶ አደሮች ለ3 ዓመታት የካሳ ባለመከፈሉ ለልመና መዳረጋቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡

አርሶ አደሮቹ ስለቅሬታቸው ምን አሉ?

“ ከቸና እስከ መካነ ኢየሱስ ከተማ ድረስ ባለው ፕሮጀክት ለተወሰደው መሬት 2014 ዓ/ም የካሳ ክፍያ ብናውቅም 40 አርሶ አደሮች ለ3 ዓመታት ካሳ አልተከፈለም፡፡

በአሰራሩ መሰረት የካሳ ክፍያ እንደወቅቱ ሁኔታ እየታዬ በየስድስት ወሩ ማሻሻያ ይደረግበታል ክፍያ ሳይፈጸም ከቆዬ። የኛ ግን ለ3 ዓመት ማሻሻያ አልተደረገበትም፡፡

ከዓመታት በፊት የተገመተው ካሳ አሁንም ባለበት ነው። ከ3 ዓመታት በፊት የነበረው የገንዘብ ዋጋ ከአሁኑ ጋር ሲነጻጸር ሰፊ ልዩነት አለው። ያም ሆኖ ግን ከዓመታት በፊት የነበረው ካሳም እየተከፈለን አይደለም፡፡

የመካነ ኢየሱስ ከተማ ነዋሪም ቤቱን ሽጦ እንዳይመገብ መስመር ዳር ሊፈርስ ምልክት ስለተደረገበት መሸጥ አይቻልም፡፡ የገጠሩ አርሶ አደርም የተወሰደብን መሬት የአትክልት ማምረቻ ጭምር ማሳ ነው፡፡

አርሶ አደሩ እስከ 3 ማሳ ነበረው በግራና ቀኝ መንገድ ፕሮጀክቱ የደረደበት፡፡ አርሶ አደሩ ወይ አርሶ አልተጠቀመ ወይ የካሳ ክፍያ አላገኘ፡፡ አትክልቱ እንኳ አድጎ ጥቅም እንዳይሰጥ በለጋው ተቀጭቷል ” ብለዋል።


በ2014 ዓ/ም በነበረው የካሳ ተመን መሰረት ከ200 ሺሕ እስከ 1 ሚሊዮን ብር በላይ የተገመተላቸው አርሶ አደሮች እንዳሉ ገልጸው፣ በአሁኑ የገንዘብ የመግዛት አቅም ዋጋ ተተምኖ በቶሎ ካሳው እንዲከፈላቸው ጠይቀዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ፣ ለምን የአርሶ አደሮቹ ካሳ በወቅቱ አልተከፈለም፣ መቼስ ይከፈላለቸዋል? ሲል የአማራ ክልል መንገዶች ባለስልጣንን ጠይቋል።

የአማራ ክልል መንገዶች ቢሮ ምን መሰለ?

“ የወሰን ማስከበር ክፍያዎች በመንግስት በጀት ከምንከፍላቸው ክፍያዎች አንዱ ነው። ግን ክፍያዎቹን በተገቢው በሚፈለገው አግባብ እየከፈልን አይደለም።

ይሄ ደግሞ የተፈጠረው ለመስሪያ ቤታችን ከመንግስት በሚለቀቀው በጀት ጋር ተያይዞ እየገጠመን ባለው የበጀት ችግር ነው።

ይሄን ችግር እናውቀዋለን። ለመፍታት እየታገልን ያለነው ነው። ስለዚህ የበጀት ችግሩ እንደተፈታልን፣ መፈታት ብቻም ሳይሆን እንደተቃለልን ቀሪ ክፍያዎችን ባለው ፕራዮሪቱ ኦርደር መሠረት እንከፍላለን ” ብሏል።

(ጉዳዩን እስከመጨረሻው የምንከታተለው ይሆናል
)

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
Please open Telegram to view this post
VIEW IN TELEGRAM
#የሠራተኞችድምጽ🔈

🔴 “ የምናደርገው አጥተን ነው ተማረን በእንባ የወጣነው። 3 ልጆች አሉኝ  በ1,000 ብር ደመወዝ ነው የምተዳደረው፤ አሁን የት እንውደቅ ? ” - የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞች

➡️ “ ፕሬዚዳንቱ ተስፋ አስቆረጠን። 'እናንተን ዩንቨርሲቲው እንጂ የቀጠራችሁ የመንግስት ሰራተኞች አይደላችሁም' አለን ” - የ1,100 ብር ደሞዝተኛ

እስከ 20 ዓመታት ' አገለገልን ' ያሉ ከ800 በላይ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምገባና የሌሎች ሠራተኞች " ዩኒቨርሲቲው ከሥራ ሊያሰናብተን ነው " ሲሉ በቲክቫህ ኢትዮጵያ በኩል ስሞታ አሰሙ።

ሠራተኞቹ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጡት ቃል በዝርዝር ምን አሉ ?

አንድ አባት ፥ “ ከ2004 ዓ/ም ጀምሮ ከከተማው ተደራጅቼ በመስተንግዶና ሁለገብ ሥራ ግቢው እንደፈለገ ነው የምሰራው። የአባቶች እግራቸው ተሰብሯል፤ ጥርሳቸው ወልቋል፤ እጃቸው በእሳት ተቃጥሏል ” ብለዋል።

“ የዩኒቨርሲቲ ዋናው ፕሬዚዳንት ‘መንግስት መዋቅር እያስተካከለ ነው። ይህ ሂደት ካለቀ በኋላ ማኀበራትን ሁሉ ያሰናብታል። መንግስት ከዚህ ግቢ አያውቃችሁም’ ብሏል። እንደ አሮጌ እቃ ቆጥረውናልና መፍትሄ የሚሰጠን የህግ አካል መጥቶ ይመልከተን ” ሲሉም ተማጽነዋል።

ልላኛው አባት፣ “ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከ16 ዓመታት በላይ ከባልደረቦቻችን ጋር እንጨት እየፈለጥን እየተሸከምን ብዙ የሥራ ጫና ነበረብን ” ሲሉ ገልጸዋል።

“ ወድቄ ከተሰበርኩ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖኛል፤ ነገር ግን ህክምና አላገኘሁም። ሦስት ልጆች አሉኝ በ1000 ብር ደመወዝ ነው የምንተዳደረው። አሁን የት እንውደቅ ? የት እንግባ ? ” ሲሉም ጠይቀዋል።

ሌላኛው ቅሬታ አቅራቢም፣ “ 9 ቤተሰብ የቤት ኪራይ እየከፈልኩ አስተዳድራለሁ። እኔ ራሴ መማር እፈልጋለሁ። ግን በገንዘብ ማነስ ምክንያት አልቻልኩም። 1,100 ብር ነው የሚከፈለኝ። ይቺን 1100 ብር ታዲያ ወስጄ ምንድን ነው የማደርጋት ? ” ሲሉ ጠይቀዋል።

ሌላኛዋ እናት፣ “ ለፍተን እየሰራን ቆይተን አሁን ሁለት ፀጉር አብቅለን በሽተኛ ከሆንን በኋላ ጅብ ይብላችሁ ጎዳና ውጡ ተብለናል።  አራት፣ አምስት ወራት የቆዩትን ቋሚ አድርጎ 20 ዓመት በላይ ቆይታ እያለን ምንም አንዳልጠቀምን ተደርገናል ” ብለዋል።

“ 7 ልጆች አሉኝ ደመወዜ 1000 ብር ነች ከሌሎቹ እኩል አድርጉን እኛም ኢትዮጵያዊ ነን፤ አዋጁ ይመለከተናል፤ ይጨምርልን ስላልን ነው ‘ውጡ’ የተባልነው አንዲያውም አረጋውያን ይደገፉ እንጂ ይጣሉ አይባልም ነበር ” ሲሉም ወቅሰዋል።

ሌላኛዋ ቅሬታ አቅራቢ፣ “ 17 ዓመት ከጅብ ጋር እየተጋፋን እንደ ሻማ ቀልጠን አገልግለናል። ደመወዝ ጭማሪ ስንጠይቅ ‘እንዲያውም እስካሁን አገልግላችኋል አንፈልጋችሁም’ ተባልን ” የሚል ወቀሳ አቅርበዋል።

አክለው፣ “ እኔስ ቆሜ በሚዲያ ተናገርሁ ስንቱ ነው እግሩ የተቀደደው! ስንቱ ነው ሰባራ ሆኖ በየቤቱ ያለው። ቋሚ ሰራተኛ አድርጉን አላልንም ደመወዝ ይጨመርልን ነው የኛ ጥያቄ ” ነው ያሉት።

ሌላኛዋ እናት፣ “ ሙሉ 30 ቀናት ነው አፈር ግጠን የምንሰራው። ስንቀጠር 330 ብር ነበር ትንሽ፣ ትንሽ እየተጨመረልን 1100 ደረሰ። በኋላ ይጨመረናል ብለን ስንጠብቅ አዲሱ ፕሬዚዳንት ጭራሽ ተስፋ አስቆረጠን። ‘እናንተን ዩንቨርስቲው ነው እንጂ የቀጠራችሁ የመንግስት ሠራተኞች አይደላችሁም’ አለን ” ሲሉ ገልጸዋል።

“ ዩኒቨርስቲው ትንሽ፣ ትንሽ እየጨመረ ቆይቷል፤ አሁንስ ለምን አይጨምርም? ኑሮ ውድነቱ በኛስ አልጨመረም ወይ? ብለን ስንጠይቅ፥ ‘እናንተን አናወቃችሁም። እንዲያውም ተንሳፋፊ ሰራተኛ ተመድቦ ይሰራል። እናንተን እናስወጣለን ብዙ ስላገለገላችሁ ይበቃችኋል’ አለን ” ብለዋል።

አክለው፣ “ የምናደርገው አጥተን ነው ተማረን በእንባ የወጣነው ” ያሉ ሲሆን፣ ልላኛው አባትም፣ “ ከ2002 ጀምሬ ነው ዩኒቨርሲቲ ላይ በመስተንግዶ የሰራሁት። በሳምንት፤ በሁለት ሳምንታት ህክምና ለልዩ ልዩ ነገሮች ይኖራሉ። ሁሉን ትተን እየሰራን ቆይተናል ” ብለዋል።

“ ልጆች እናስተምራለን፤ የቤት ኪራይ አንከፍላለን በወር 1,100 በቀን 33 ብር እየተከፈለው በዚህ ኑሮ ውድነት ሰው እንዴት ይኖራል? ብለን ጥያቄ ስናቀርብ ‘በኔ በኩል ጨርሻለሁ ወደ ሚመለከተው ሂዱ የምታመጡት ነገር የለም’ ነው ያለን ፕሬዝዳንቱ ” ሲሉም አማረዋል። 

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ለቅሬታው ምላሽ ለመጠየቅ ወደ ዩኒቨርሲቲው ፕሬዜዳንትና ምክትል ፕሬዜዳንት ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ለጊዜው ስልክ ለማንሳት ፈቃደኛ አልሆኑም።

(ጥረቱ ይቀጥላል)

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
Please open Telegram to view this post
VIEW IN TELEGRAM
TIKVAH-ETHIOPIA
Photo
#Update

🔴 " ሙሉ ፓትሮል መኪና መጣብን፡፡ እኛ ሮጠን አመለጥን ሌሎች 5 ሰዎች ታስረዋል " - የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞች

➡️ " እየለፉ እስከሆነ ድረስ ቢጨመርላቸው ደስ ይለናል " - የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ

⚫️ " የማውቀው ጉዳይ የለም " - የክልሉ ፓሊስ ኮሚሽን

ከማኀበራት ተውጣጥተው በሀዋሳ የኒቨርሲቲ በምገባና ሌሎች ስራዎች ለዓመታት ሰራን ያሉ ወደ 800 ሠራተኞች ደመወዝ እንዲጨመርና ቋሚ ቅጥረኛ እንዲሆኑ ጥያቄ በማቅረባቸው፣ ዩኒቨርሲቲው ከሥራ ሊያሰናብታቸው መሆኑን በቲክቫህ ኢትዮጵያ በኩል አቤት ብለው ነበር።

ሠራተኞቹ ዛሬ በሰጡን ቃልስ ምን አሉ ?

“ ደመወዝን በተመለከተ ቅሬችንን ለመግለጥ ወደ ደቡብ ኤፍኤፍ እየሄድን በነበረበት የተወሰኑ ሰዎች ታስረዋል መብታቸውን ስለጠቁ ታስረዋል፡፡ አንዱ ታሳሪ ታሟል፡፡

ጠዋት ደቡብ ኤፍኤም ቀጥሮን ነበር፡፡ 2 ሰዓት ተኩል ወደ ጣቢያው ስንሄድ ሙሉ ፓትሮል መኪና መጣብን፡፡ እኛ ሮጠን አመለጥን ሌሎች 5 ሰዎች ታደስረዋል፡፡ ጠዋት ነው የታሰሩት አሁን ስንሄድ ቃላቸውን የሚቀበላቸው የለም። እኛንም እየፈለጉን ነው ካፓስ ውጪ ነን። 

ሰዎቹ የታሰሩት ሀዋሳ 01 ፖሊስ ጣቢያ ነው፡፡ ምንም አላጠፋንም፡፡ ‘ለምን ተሰባሰባችሁ’? ሲሉን የደመወዝ ጭማሪ አልደረሰንም፡፡ በ1,000 ብር ደመወዝ እየሰራን ኑሮ ውድነቱን መቋቋም አልቻልንም፡፡ መንግስት እንዲመለከተን ለሚዲያ ቃላችንን ልንሰጥ ነው የመጣነው አልናቸው፡፡

ከዚያ በኋላ ‘እንዴት ስማችን ይጠፋል? ለምንድን ነው የምታስተላልፉት’? ብለው ነው ወንዶቹን አተኩረው ያሰሯቸው። የታሰሩት ሠራተኞች እንጨት ሲፈልጡ ለትርፍ አንጀት በሽታ ተጋልጠው ቀዶ ጥገና የተሰሩ ናቸው፡፡ አንዱ መኪና ላይ ሲወረውሩት ራሱን አያውቅም።

መንግስት ይየን፡፡ ፍትህ ይደረግልን፡፡ የኑሮ ውድነት እኛን አልነካም? እኛ ልጆች የሉንም? ለምንድን ነው መንግስት የማያየን? የኑሮ ወድነቱን አልቻልንም፡፡ ተንከራተን ነው የምንኖረው፡፡ ልጆቻችን እየተራቡ፣ እየተጠሙ ነው፡፡

24 ሰዓት ነው ግቢ ውስጥ የምንሰራው፡፡ ከግቢ ወጥተን ሌላ ሥራ ለመስራትም ጊዜ የለንም፡፡ ሁሉም በችግር ላይ ነው። በዛ ላይ ወጥ የተደፋባቸው፣ እጃቸውን ማሽን የቆረጣቸው አሉ። አካል ጉዳተኞቹንም ለማሳየት ነበር ወደ ሚዲያ የሄድነው፡፡ ግን መብታችን ተረግጧል፡፡ ዲሞክራሲም የለም፡፡

አካል ጉዳተኞች 50 በላይ ይሆናሉ፡፡ እናቶች መንቀሳቀስ ስለማይችሉ ቤት ውስጥ ነው ያሉት፡፡ የሚያሰሩት ሰዎችን 600 ብር ቀጥረው ነው፡፡ መስራት ስላማችሉ፡፡ ከታሰረው እንዱ ራሱ ወጥ ተደፍቶበት እግሩ ተቃጥሏል፡፡

እንጨት ከጫካ ተሸክመን አምጥተን ፈልጠን በዬኩሽናው እናደርስ ነበር። እንደዚህ ደክሞን ውለን የምንታጠብበት ሳሙና አልነበረንም። ችግር ከትክሻችን አልወርድ አለ። 

ለሌሎች ደመወዝ ሲጨመር የኛስ ድካም ለምን አይታይም? ልጆች እናስተምራለን፣ የቤት ኪራይ አለብን። 'ደመወዝ ተጨምሯል' ሲባልም የቤት ኪራይ ተጨምሮብን 'ቅድሚያ ካልከፈላችሁ ውጡ’ እየተባልን ነው፤ ተጨንቀናል ” ሲሉ ቅሬታ አቅራቢዎች አማረዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያም፣ የሠራተኞችን ቅሬታ ይዞ ፤ ሰዎቹ የመብት ጥያቄ ስላነሱ ለምን ታሰሩ ? ይህን ማድረግ አግባብ ነው ? ሲል የሲዳማ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮን ጠይቋል።

አንድ የቢሮው አካል በሰጡት ምላሽ፣ የደመወዝ ጭማሬና ቋሚ ሰራተኛ መሆንን በተመለከተ ዩኒቨርሲቲው የራሱ መተዳደሪያ ደንብ እንዳለው፣ ጭማሬው ለቋሚ ሠራተኞች እንጅ ለጊዜያዊ እንደማይሆን ገልጸዋል፡፡

ቲክቫህ ኢትዮጵያም፣ ለሰዎቹ ደመወዝ የመጨመርና ቋሚ ሠራተኛ ማድረግን የሚመለከተው ዩኒቨርሲቲው ሆኖ እያለ፣ ሠራተኞቹ የመብት ጥያቄ በማቅረባቸው መታሰታቸው አግባብ ነው ? ሲል ለእኝሁ አካል በድጋሚ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

እሳቸው በምላሻቸው፣ ከክልል ይታሰሩ እንዳልተባለ ገልጸው፣ " አንተ እንዳልከው እኛ ደመወዝ ይጨመርላቸው፤ አይጨመርላቸው የመተዳደሪያ ደንብ ስላላቸው እነርሱ ናቸው የሚያስተካክሉት " ብለዋል፡፡

" ቢጨምሩላቸው እኛም ደስ ይለናል፡፡ እየለፉ እስከሆነ ድረስ ቢጨመርላቸው ደስ ይለናል፡፡ ግን እነዚህ ሰዎች ታስረዋል ? ማነው ያሰራቸው ? የሚለውን ለመጠየቅ እየሞከርኩኝ ነው፡፡ የሀዋሳ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ናቸው፡፡ ሲወጡ እንዴት ታሰሩ ? የሚለውን አጣራለሁ " ብለዋል፡፡

በተጨማሪም፣ ሠራተኞችን ለምን እንደታሰሩ ማብራሪያ  የጠየቅናቸው የሲዳማ ክልል ፓሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ካሳ ጩቦ በሰጡን ቃል፣ " የማውቀው ነገር የለም " የሚል አጭር ምላሽ ሰጥተዋል።
 
(የክልሉ ፓሊስና ጸጥታ ቢሮ ተጨማሪ አጥጋቢ ምላሽ  ከሰጡን የምናቀርብ ሲሆን፣ ጉዳዩንም እስከ ጥግ እንከታተለዋልን)

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
" በስም ከተለዩት ግለሰቦች መካከል ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ዜጎችም ይገኙበታል " -የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ

የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ከ3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ የታክስ ዕዳ ያለባቸው 62 ግብር ከፋዮች ከሀገር እንዳይወጡ የእግድ ትዕዛዝ ማስተላለፉን ገልጿል፡፡

እግድ የተጣለባቸው 62 ግለሰቦች በተደጋጋሚ ጥሪ ቢደረግላቸውም ዕዳቸውን ለመክፈል  ፈቃደኛ ያልሆኑ ናቸው ተብሏል።

" በስም ከተለዩት ግለሰቦች መካከል ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ዜጎችም ይገኙበታል ዕዳቸውን የማይከፍሉ ከሆነም አዋጁ በሰጠን ሥልጣን መሰረትም በቀጣይ የንብረት እግድ እና ንብረታቸውን በሃራጅ የመሸጥ እርምጃዎች ይወሰዳሉ " ሲሉ የቢሮው የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

ቢሮው በታክስ አስተዳደር አዋጅ 983/2008 አንቀፅ 44 ንዑስ አንቀፅ ከ1-3 ለተቋሙ በተሰጠ ስልጣን መሰረት ከሀገር እንዳይወጡ እግድ የተጣለባቸው ግለሰቦች ስም ዝርዝር ለፌዴራል የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ማስተላለፉን አሳውቋል፡፡

የ62ቱ ግለሰቦች ስም ዝርዝር ለፌዴራል የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የተላከው በትላንትናው ዕለት ነው።

አቶ ሰውነት " በህጉ መሰረት የተቀመጠ ቀነ ገደብ አለ በአዋጁ በተቀመጠው ቀነ ገደብ መሰረት መጥተው እስካልከፈሉ ድረስ ለእዳው ማካካሻ በሚሆን መሰረት ንብረታቸው በሃራጅ ተሽጦ እዳው ይሸፈናል " ብለዋል።

ቢሮው የግብር ዕዳቸውን ሳይወጡ የሚሰወሩ ግብር ከፋዮችን በመከታተል ግዴታቸውን እንዲወጡ ለማስቻል የዕዳ ክትትልና አስተዳደር የስራ ክፍልን በ2017 በጀት ዓመት እንደ አዲስ አዋቅሯል።

በዚህም መሰረት ባለፉት 6 ወራት ከ 6.4 ቢሊዮን ብር በላይ የታክስ እዳ መሰብሰቡን አቶ ሰውነት ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
ከጀርባዋ " ኤሌክትሮኒክ ቁስ ተሸክማ ስትበር ተያዘች " የተባለችው ወፍ ምንድነች ?

🔴 “ ምርመራ እየተደረገ ነው ፤ ገና አላለቀም ” - የቤንሻንጉል ክልል ፓሊስ ኮሚሽን

➡️ “ ምርመራ እየተደረገ ነው። ሲያልቅ እናሳውቃለን ” - የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን እና ሰላምና ጸጥታ ቢሮ 


በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማኦና ኮሞ ልዩ ወረዳ ጉሬ ቀበሌ “ በጀርባዋ ላይ ኤሌክቶርኒክስ ቁስ ተገጥሞባታል ” የተባለችና ከወትሮው ለየት ያለች ወፍ ስትበር መያዟን ቲክቫህ ኢትዮጵያ ከአካባቢው ነዋሪዎች ሰምቷል።

በገለጻው መሠረት፣ ወፏ በጉሬ ቀበሌ ሰማይ ስር ስትበር የተገኘችው ከቀናት በፊት ሲሆን፣ ኤሌክትሮኒክስ ቁስ የተገጠመላት ከመሆኗ ባሻገር፣ ሙሉ አካሏ በአርቲፊሻል የተሞላ፣ በሁለት እግሯቿም ቀለበቶች እንዳላት ተመላክቷል።

እንዲህ አይነት ወፍ ከዚህ በፊት በአካባቢው ዝር ብሎ እንደማያውቅ የተናገሩት ነዋሪዎች በተለይ ወፏ እግር ላይ ያሉት ቀለበቶችና በጀርባዋ ተገጥሞላታል የተባለው ኤሌክትሮኒክ ቁስ “ ምን የያዘ ነው ? ” በሚል ስጋትን እንደደቀነባቸው ጠቁመዋል።

አንዳንዶችም ጉዳዩ “ ከህዳሴ ግድቡ ጋ ሊገናኝ ይችል ይሆን ? ” የሚል መላምት ሲያስቀምጡም ቲክቫህ ኢትዮጵያ ተመልክቷል።

በተለይም ከጸጥታ ጋር በተያያዘ ወፏ ላይ ምርመራ ለማድረግ በጸጥታ አካላት ወፏ ወደ አሶሳ ከተማ ሳትወሰድ እንዳልቀረች ተነግሯል።

በዚህም ስለጉዳዩ የተጠየቅነው የአሶሳ ፓሊስ መምሪያ፣ ጉዳዩን እንደሰማ፣ ነገር ግን ሁነቱ ከከተማው ውጪ በመሆኑ ምርመራው እንደማይመለከተው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጿል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ በተጨማሪም፣ በማኦና ኮሞ ልዩ ወረዳ ሰማይ ስር ስትበር ታየች የተባለችው ቀለበትና ኤሌክትሮኒክ ቁስ በጀርባዋ እንዳላት የተነገረላት ወፍን ምንነት አውቀው እንደሆን የክልሉ ፓሊስ፣ ኮሚዩኒኬሽን፣ ሰላምና ጸጥታ ቢሮዎችን ጠይቋል።

አንድ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ፓሊስ ኮሚሽን ከፍተኛ አመራር በሰጡት ምላሽ፣ “ መከላከያ ጋር ነው፤ ምርመራ እየተካሄደ ያለው። ምርመራው ገና ለላለቀም ” ሲሉ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል። 

ስለጉዳዩ የጠየቅናቸው አንድ የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አካል ደግሞ መረጃው እንደደረሳቸው ገልጸው፣ “ ምርመራ እየተደረገ ነው። ሲያልቅ እናሳውቃለን ” የሚል ምላሽ ሰጥተውናል።

ተመሳሳይ ጥያቄ ያቀረብንለት የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ በበኩሉ፣ ወፏን በተመለከተ ምርመራ እየተደረገ እንደሆነ፣ ምርመራው ሲጠናቀቅ ማብራሪያ እንደሚሰጠን ቃል ገብቷል።


(ጉዳዩን ተከታትለን በቀጣይ መረጃ የምናደርሳችሁ ይሆናል)

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
#Update 🔴 " ሙሉ ፓትሮል መኪና መጣብን፡፡ እኛ ሮጠን አመለጥን ሌሎች 5 ሰዎች ታስረዋል " - የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞች ➡️ " እየለፉ እስከሆነ ድረስ ቢጨመርላቸው ደስ ይለናል " - የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ⚫️ " የማውቀው ጉዳይ የለም " - የክልሉ ፓሊስ ኮሚሽን ከማኀበራት ተውጣጥተው በሀዋሳ የኒቨርሲቲ በምገባና ሌሎች ስራዎች ለዓመታት ሰራን ያሉ ወደ 800 ሠራተኞች ደመወዝ እንዲጨመርና…
#Update

🔴 “ የታሰሩት ተፈትተዋል፡፡ የመብት ጥያቄ በማቅረብችን ነው ያሰሩን፡፡ 10 ሠራተኞች ሥራ ተከልክለናል ” - የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞች

➡️ “ ቅሬታ እንዳለባቸው አውቃለሁ፡፡ ያንን ማሰማት መብታቸው ነው፡፡ የሰሩት ወንጀል የለም ” - የከተማው ጸጥታ መምሪያ

በዛ ቢባል 1,100 ብር ደመወዝተኛ ለ20 ዓመታት ምገባና ሌሎች ሥራዎችን የሰሩ 800 የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ እንዲደረግላቸው ዩኒቨርሲቲውን ሲጠይቁ ‘እንዲያውም አሰናብታችኋላሁ’ እንዳላቸው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ከቀናት በፊት ተናግረው ነበር።

ሠራተኞቹ ከዚያ በኋላ በገለጹት መሰረት፣ ቅሬታቸውን ለሚዲያ ለማቅረብ በሄዱበት ወቅት ደግሞ የተወሰኑት ሠራተኞች በፖሊስ እንደታሰሩ ነበር የነገሩን።

የሲዳማ ክልል ጸጥታ ቢሮ ጉዳዩን እንደሚያጣራና ሠራተኞቹ ደመወዝ ቢጨመርላቸውም እንደማይከፋው፣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ጉዳዩን እንደማያውቅ ስለጉዳዩ ከቲክቫህ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተው ነበር።

ታሰሩ የተባሉት ሠራተኞች ተፈቱ ?

የታሰሩት ሠራተኞች ትላንት ጠዋት በዋስ እንደተፈቱ፣ ገና ወደ ሥራ እንዳልገቡ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ታስረው ከነበሩና ከቅሬታ አቅራቢ ሠራተኞቹ ገለጻ ለማወቅ ችሏል፡፡

ሠራተኞቹ በሰጡን ቃል፣ “የታሰሩት ተፈትተዋል፡፡ የመብት ጥያቄ በማቅረብችን ነው ያሰሩን፡፡ ከ10 በላይ ሠራተኞች ሥራ ተከልክለናል” ነው ያሉት።

የመብት ጥያቄ ለማቅረብ ከመሞከር ውጪ ጥፋት እንዳልፈጸሙ፣ ሆኖም በዩኒቨርሲቲ በሚገኘው 01 ቀበሌ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው ከቆዩ በኋላ በመታወቂያ ዋስ እንደተለቀቁ ሠራተኞቹ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል፣ ቅሬታ ካቀረቡት የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች መካከል 10 የሚሆኑት “ወደ ዩኒቨርሲቲው ለሥራ አትግቡ” ተብለው እንደተከለኩ ገልጸው፣ መብታቸው እንዲከበርላቸው በድጋሚ ጠይቀዋል፡፡

ታሳሪዎቹን በተመለከተ ምላሽ እንዲሰጥ ሰሞኑን ቲክቫህ ኢትዮጵያ ሲጠይቀው የነበረው የሀዋሳ ከተማ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ፣ ጉዳዩን አጣርቶ ምላሽ ለመስጠት ገልጾ ነበር፡፡

መምሪያው ትላንት በሰጠን ምላሽ፣ “ምንም የታሰረ አካል የለም፡፡ የተፈጠረ ነገርም የለምኮ ለምንድን ነው የሚያታሰሩት?” ብሏል።

“ ቅሬታ እንዳለባቸው አውቃለሁ፡፡ ያንን ማሰማት መብታቸው ነው፡፡ የሰሩት ወንጀል የለም፡፡ የሚያሳስራቸው ጉዳይም የለም ” ሲል ተናግሯል።

የተፈጠረ ነገርማ አለ፤ ሠራተኞች እንደታሰሩ ተናግረዋል፣ ለመሆኑ ከከተማው 01 ቀበሌ ፖሊስ ጣቢያ ሄዳችሁ አጣርታችሁ ነበር ? ስንል ላቀረብለት ጥያቄ ደግሞ፣ “ ቼክ አድረገናል፡፡ ወንጀል የለባቸውም፡፡ ዩኒቨርሲቲውም ለኛ ያመለከተን ጉዳይ የለም ” ብሏል።

ሠራተኞቹ በበኩላቸው፣ “ እነርሱማ እውነት ነው አይሉም ” ሲሉ ወቅሰዋል።

(ክትትሉ ይቀጥላል)


#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
ከጀርባዋ " ኤሌክትሮኒክ ቁስ ተሸክማ ስትበር ተያዘች " የተባለችው ወፍ ምንድነች ? 🔴 “ ምርመራ እየተደረገ ነው ፤ ገና አላለቀም ” - የቤንሻንጉል ክልል ፓሊስ ኮሚሽን ➡️ “ ምርመራ እየተደረገ ነው። ሲያልቅ እናሳውቃለን ” - የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን እና ሰላምና ጸጥታ ቢሮ  በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማኦና ኮሞ ልዩ ወረዳ ጉሬ ቀበሌ “ በጀርባዋ ላይ ኤሌክቶርኒክስ ቁስ ተገጥሞባታል ” የተባለችና…
#Update

“በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አዕዋፋት ይመጣሉ። ባለፍኩበት የስራ ዘመን እንደዚህ አይነቱን አሰራር ለስለላ ተጠቅመውበት አያውቁም” - በዘርፉ 40 ዓመታት የሰሩ የአዕዋፍ ሳይንቲስት

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማኦ እና ኮሞ ልዩ ወረዳ በጀርባዋ የኤሌክትሮኒክ ቁስ ተሸክማ ስትበር ተገኘች የተባለችው ወፍ የብዙዎችን ቀልብ ስባለች።

ብዙዎች “ለስለላ የተላከች ወፍ ነች” የሚል ስጋታቸውን በማኀበራዊ ሚዲያ ሲያንጸባርቁ የተስተዋሉ ሲሆን፣ ቲክቫህ ኢትዮጵያም የክልሉን አካላት ስለጉዳዩ ጠይቆ ገና በምርመራ መሆናቸውን ከመግለጽ ውጪ ያሉት የለም።

የወፏ ጉዳይ እውነትም ስለላ ሊሆን ይችላል ይሆን ? እስከዛሬ በነበሩ መሰል ክስተቶች በወፍ አማካኝነት ስለላ ተደርጎ ያውቃል ? ስንል የአዕዋፋት ሳይንቲስት አቶ ይልማ ደለለኝን ማብራሪያ ጠይቋል። 

በዘርፉ የ40 ዓመት ልምድ ያላቸው ባለሙያ ምን መለሱ ?

አሁን በግላቸው የአካባቢ ጥበቃ ላይ፣ ከዚህ ቀደም በዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን የሰሩት አቶ ይልማ እንዳሉት፣ ሰምንኛው የወፏ ጉዳይ በየዓመቱ የሚስተዋልና ሥጋት ሊደቅን የማይችል የተለመደ ሁነት ነው።

ባለሙያው፣ ከጀርባቸው ሶላር ጂፒኤስ፣ ከእግራቸው ቀለበት የተገጠመላቸው ወፎች የሆነ ወቅት ቅዝቃዜን በመሸሽ ከአውሮፓ ሀገራት 7000 ድረስ ኪሎ ሜትር አቋርጠው በየዓመቱ የሚመጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ወፎች ላይ ቀለበትና ሶላር ጂፒኤስ ገጥሞ መላክ ታዲያ ለምን አስፈለገ? የሚለውን ጥያቄ ሲያብራሩም፣ ከጀርባቸው ያለው ሶላር ጂፒኤስ ወፎች የት እንዳሉ፣ በምን ያህል ከፍታ እየበረሩ እንደሆነ፣ ወደየትኛው አገር እንደሄዱ አውሮፓያውያኑ የሚከታተሉበት እንደሆነ አስረድተዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ፣ ባለዎት ልምድ መሰረትና እንደብዙኅኑ ስጋት ቀለበትና ሶላር ጂፒኤስ በተገጠመላቸው ወፎች ስለላ ተደርጎ አያውቅም? የሚል ጥያቄ ለባለሙያው አቅርቧል።

አቶ ይልማ ምን መለሱ ?

ሰዎች ይህንን ከፖለቲካ ጋር ያያይዙታል። ነገር ግን ፒዩርሊ የሳይንስ ስራ ነው። እኔም ብዙ ጊዜ ወፎች ላይ ቀለበትና ጂፒኤስ ትራከር አስሪያለሁ። 

ኢትዮጵያ እንኳን በሚመጡበት ወቅት ያን ቀለበትና ጂፒኤስ አስረን የት ድረስ እንደሚሄዱ የምንከታትልበት ሲስተም አለ። ሳይንቲስቶች ከእውቀት ጉጉት የሚያደርጉት ነው እንጂ በፍፁም የስለላ ተግባር እንዳልሆነ ነው የምረዳው። 

ያው ኢትዮጵያ ውስጥ ያን ያክል ጥልቅ እውቀት ስለሌለና አሁን ያለንበት የሰላም ሁኔታ ጋር ተደማምሮ ሰዎች እንደዚህ እንዲያስቡ አድርጓቸዋል። እውነት ለመናገር ለስለላ ቢሆን ኖሮ ወፍ ሳይሆን ድሮን ላይ በተገጠመ ነበር። ምክንያቱም የተፈጥሮ ወፍን እንቅስቃሴ መቆጣጠር አይቻልም።

በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አዕዋፋት ይመጣሉ። እነርሱ (አውሮፓውያኑ) ከኛ የተሻለ ፍለጎቱ፣ እውቀቱ፣ አቆርቦቱ፣ የገንዘብ አቅሙም ስላላቸው በአዕዋፍ እንደዚህ ያደርጋሉ እንደዚህ ዓይነቱ ስራ ደግሞ ከገንዘብ በተጨማሪ ብዙ ጊዜና ክትትል ይፈልጋል።

ከዚህ ቀደምም በደርግ ዘመን የኢትዮ - ኤርትራና የካራማራ ጦርነት በነበረበት ወቅት ደርግም ደግሞ ኮሚኒስት ከመሆኑ የተነሳ ከአሜሪካና ከአውሮፖ ሀገራት ‘የተላከ ሰላይ ነው’ በሚል ብዙ ጭንቅላት የሚያዞር ችግር ነበር፤ እኛም ይህን ለማስረዳት ሞክረናል። 

አሁንም ሰዎች ይህን ቢሉ እኔ አልፈርድም ምክንያቱም እኛ ባለሙያዎችም ብንሆን እንደዚህ አይነቱን ነገር ቀድመን ለማህበረሰቡ ማሳወቅ ይጠበቅብናል።

ባለፍኩበት የስራ ዘመን እንደዚህ አይነቱን አሰራር ለስለላ ብዙም ተጠቅመውበት አያውቁም። በእርግጥ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የወፎች እግር መልዕክት ይደረግላቸውና መልዕክት የሚላላኩትን ሰዎች ቤት እርግቧ ስለምታውቅ ከአንዱ ወደ ልላኛው ስታስተላልፋል።

በዛ ጊዜ የተጠቀለለ ወረቀት በትንሽየ እቃ አድርገው በወፍ ጀርባ ላይ ያደርጉትና ለሚፈለገው አካል ይደርስ ነበር። ምክንያቱም ወፍ ላይ መልዕክት ይኖራል ተብሎ ስለማታይ ጠላት ባለበት ጎራም አልፈው ወገን ጋር ሊያደርሱ ይችላሉ።

በወፎች ስለሚደረገው ስለላ ይህን ብቻ ነው የማውቀው ይኸውም ያኔ እንደአሁኑ ቴሌግራም፣ ፌስቡክን የመሳሰሉ የመልዕክት መለዋወጫዎች ስላልነበሩ ነው። አሁን ወፎች ለስላላ ጥቅም አይውሉም፤ አንዲያውም ጂፒኤስ የሚደረግባቸው ወፎች ረጅም ርቀት በመጓዝ በመጓዛቸው፣ በርሀብና በጥም ምክንያት 75% ይሞታሉ” ብለዋል።

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
TIKVAH-ETHIOPIA
#Update 🔴 “ መንግስት እንዲመጡ ስላላደረገ ከእገታው የወጡት ኢትዮጵያዊያንም በፓሊስ ተመልሰው እየተወሰዱ ነው። እስካሁን ሰባት ልጆች ተወስደዋል ” - ቤተሰብ 🔵 “ እኛ ዜጎች አይደለንም እንዴ? መንግስት ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ትዕዛዝ መስጠት አይችልም? ” - ኢትዮጵያዊ በታይላንድ ➡️ “ ልጆቻችን በረሃብ ሊያልቁብን ነው ” - የወላጆች ኮሚቴ ሰርተው ለመለወጥ ሲሉ ተታለው ወደ ታይላንድ…
🔈#የኢትዮጵያውያንድምጽ

“ ወደ 29 ኢትዮጵያውያን ይበልጥ የከፋ ቦታ ተወስደዋል። ” - ኢትዮጵያዊያን በማይናማር

ካሉበት ችግር እንዲያወጣቸው መንግስትን በተደጋጋሚ የተማጸኑ ፣ ማይናማር “ ታይሻንግ ካምፕ ” ታግተው የነበሩ 29 ኢትዮጵያውያን እስከዛሬ ሲደርስባቸው ከነበረው የከፋ ስቃይ ወዳለበት ስፍራ ተገደው መወሰዳቸውን ጓደኞቻቸው ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናገሩ።

የተወሰዱት “ ዋልዋይ ” የተሰኘ ማይናማር ላይ ያለ ቦታ እንደሆነ፣ የድረሱልን ተማጽኖ ቢያስሙም የሚደርስላቸው ባለመገኘቱ ራሳቸውን እስከማጥፋት ሙከራ እያደረጉ እንዳሉ ታውቋል።

በአካባቢው ባሉ ካምፓች የነበሩ ሌሎች ሰዎች ከእገታ እየወጡ እንደሆነ፣ " ዋልዋይ " ካምፕ የሚገኙትን ታጋቾች ግን እንዳይወጡ አጋቾቹ በድብቅ እንደያዟቸው ተመልክቷል።

ኢትዮጵያዊያኑ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በተጨማሪ ምን አሉ ?

“ በማይናማር ካምፕ የነበሩ 29 ኢትዮጵውያን ካምፓኒው ‘ወደ ሌላ ቦታ ልውስዳችሁ’ ሲላቸው ለደኀነታቸው አስተማማኝ ስላልሆነ እዚሁ ነው መቆት የምንፈልገው ብለው ነበር፡፡

ነገር ግን ካምፓኒው የጸጥታ ኃይሎችን ወዳነበሩበት ካምፕ በማምጣት እጃቸውን በግዴታ እየጎተተ በመኪና አሳፍሮ በማይናማር 'ዋልዋይ' የሚባል ቦታ ወስዷቸዋል፡፡

የተወሰዱት ገና አዲስ በመሰራት ባለ ኮምፓውንድ ነውና በጣም ከፍተኛ የሆነ ስቃይ እየደረሰባቸው ይገኛሉ፡፡ ኮምፓውንዱ ህግ እና ስርዓት የለውም። በጋንግስተሮች ብቻ የሚተዳደር ነው። ለደኅንነታቸው የሚጮህላቸው የለም።

ሴቶችን ፀጉራቸውን ላጭተዋቸዋል። ወንዶችና ሴቶችን በኤሌክትሪክ ይገርፏቸዋል፤ በጨለማ ክፍል በማስገባት ከሦስት ቀናት በላይ ምግብ በመከልከል በሰንሰለት ያንጠለጥሏቸዋል።

እናም በማይናማር የነበሩ ወደ 29 ኢትዮጵያውያን ይበልጥ የከፋ ቦታ ተወስደዋል። እንዲያውም ራሳቸውን ለማጥፋት ሙከራ እያደረጉ ነው። በሰጡን መረጃ መሰረት።

እዚያ ከሄዱ በኋላ ይበልጥ ከባድ ችግር እየገጠማቸው ነው። ለካምፓኒው ሥራ ቢሰሩም ባይሰሩም ሁሌም ይቀጠቀጣሉ፡፡ ተስፋ ወደ መቁረጥ ደርሰዋል፡፡ የተወሰኑ ሰዎች ራሳቸውን የማጥፋት ሙከራ አድርገዋከል ” ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል፥ በማይናማር ታግተው አስከፊ ጊዜ ያሳለፉና ከወር በፊት ከእገታ የወጡ፣ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የኢትዮጵያ መንግስትን የቪዛና ሌሎች ጉዳዮች ይሁንታ እየጠበቁ ታይላንድ ከሚገኙ ከ250 በላይ ዜጎች መካከል ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የተረጋገጠላቸው ለመመለስ ትኬት ያላቸው 40 ሰዎች ብቻ መሆናቸውን ኢትዮጵያውያኑ ነግረውናል፡፡

ሌሎች ወደ ኢትዮጵያ መግባት የሚችሉት በራሳቸው ሙሉ ወጪ ትኬት ሲቆርጡ መሆኑን እንደተናገሩ፣ የደርሶ መልስ ቪዛና ለትኬት መቁረጫ ገንዘብ የሌላቸው በርካቶች ጭንቀት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

#TikvahEthiopiaFamilyAA

@tikvahethiopia
Please open Telegram to view this post
VIEW IN TELEGRAM