እቅበተ ተዋሕዶ
96 subscribers
113 photos
49 links
ይህ ኦርቶዶክሳዊ የእቅበተ እምነት ተዋስኦዎች የሚቀርቡበት ገጽ ነው።
加入频道
✍️ዓመቱን ጠብቀው ክህደታቸውን ደግመውታል✍️
ድጋሜ መላእከ ሞትን እየጠሩት ነው።
+++
ከሐዲዎቹ የኦሮሚያ ተወካይ ነን ባይ ሕገወጦች በፕራይምና ኦቢኤስ ሚዲያዎች ቀርበው #መግለጫ ተሰጥተዋል። ጋዜጣዊ መግለጫውን በንባብ ያቀረቡት ገብረ ማርያም ነጋሳ በቋንቋችን ለመማር እና በነጻነት ለማምለክ ለዘመናት መከልከላችን ይታወሳል ብለው #የእናት ጡት ነካሽነታቸውን ቀጥለውበታል።
እንደሚታወቀው የቤተ ክርስትያኗን ዶግማና #ቀኖና በጣሰ መንገድ የዛሬ ዓመት ጥር 14 ቀን 2015 ዓ. ምሕረት ሕገ ወጥ ሲመተ ጳጳስ ማካሄዱንና የብሔር ብሔረሰቦችን ሲኖዶስ ብሎ መፈንቅለ ሲኖዶስ ማወጁን የምናስታውሰው ነው።
"መንግስትም የህዝቡን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት ስለነበረበት ነገሩ በእርቅ እንዲያልቅ ለማድረግ ወስኖ እኛም ተቀብለናል፤ ይሁንና መንግስትን በመሸንገል ሐምሌ 2015 ጥያቄያችን ተዳፍኖ አልፏል" ብሏል የከሐዲው ስብስብ።
#ለትግራይ ተፈቅዷል የአማራም ህዝብም ሲኖዶስ አለው ስለምን ኦሮሞ ህዝብ በራሱ ቋንቋ ማምለክ ይከለከላል ሲል ዓይን ያወጣ ክህደቱን ደግሞታል። ለ5 ኪሎ ሲኖዶስ መላም የኦሮሞ ህዝብ እንዳይገዛ ጥሪ እናስተላልፋለን ብሏል የከሐዲዎች ስብስብ።
የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ምንም ዓይነት #ቀለም ያለው ባንዲራም ሆነ ምልክት ስለሌላት በኦሮምያ ምድር ላይ የማንንም የፖለቲካ ፖርቲ ባንዲራ በቤተክርስትያን ሽፋን እንዳይውለበለብ፣ እንዳይሰቀል የሚል አዋጅ አስተላልፏል።
በመጨረሻም፣ የኦሮሚያ ቤተ ክህነት የወለደው የዘውግ ስብስብ መንግስት ጥያቄው የሕዝብ መሆኑን አውቆ #ከሕገ ወጥ ሲኖዶሱ ጎን ይቆም ዘንድ ክህደታዊ ተማጽኖ ለአለቆቹ አቅርቧል።
***
ይህ እንደሚመጣ እናውቅ ነበር። የተሰጠው መፍትሔ ስር ነቀል አልነበረምና።
ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል መጽሐፋቸውን ይዘው እንዳይወጡ ተከልክለዋል። *** ትናንት ማታ በ19/05/2016 ዓ.ም ወደ አሜሪካ ለሕክምና ለመሄድ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ በአየር መንገዱ ያሉ የደኅንነት አካላት ከቤተክህነት በደብዳቤ ተፈቅዶላቸው የያዙትን 837 መጽሐፍ ቀምተው ወስደውታል። ችግሩ ምንድን ነው ብለው ሲጠይቁም የታዘዝነው ከላይ ነው የሚል መልስ ተሰጥቷቸዋል። ይህ የሚያሳየው የቤተክህነቱን ሰዎች ማንገላታትና፣ ንብረቶቻቸውን መቀማትና ደብዳቤዎቻቸውን ማጣጣል እንደ መቀጣጫ እየወሰዱት መሆኑን  ነው።

ይህ ባለፈው ሳምንት በብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የተደረገው ቅሚያ ነው ትናንትም በብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የተደገመው ።
#ቤተ ክርስቲያንን መድፈር ዋጋ ያስከፍላል!"
ሀገር ሲጠፋ #ጃርት ያበቅላል ያለው ማን ነበር ? የሆነ አካልን ከሥርዓቱ ገለል አድርጎ ፣የራስን ዘውግ ለመተካት የተካሄደው የድንቁርና ጥግ የት እንደሚያደርስ አንዱ ማሳያ ይህ ነው ።
በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት ኦርቶዶክስ ተኮር በሆኑ ጥቃቶች ባሳለፍነው ጳጉሜ 1 ቀን 2016 ዓ.ም 5 ኦርቶዶክሳውያን ተገደሉ።

በሮቤ ወረዳ ቤተ ክህነት ጄና ገዳምሳ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለምና ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን 5 ምእመናን ተገድለው ሁለቱ ደግሞ እስካሁን የደረሱበት እንዳልታወቀ የአካባቢው ምእመናን ለማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

ይህ ኦርቶዶክሳዊ ተኮር ጥቃት ከ 8 ወራት በላይ በአስከፊ ሁኔታ መቀጠሉ እና ምእመናን እየታገቱ ከ600 ሺህ ብር በላይ እንደሚጠየቁ ከቦታው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ።

በአሁኑ ሠዓት ኦርቶዶክሳውያን ቤት ንብረታቸው እየተቃጠለና ቀያቸውን ጥለው እየተሰደዱ እንደሚገኙም ተጠቁሟል።

ይህንን ጥቃት ለማስቆም ሰሞኑን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ወደ ቦታው መግባቱን የጠቀሱት አስተያየት ሰጭዎች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ጥረት እየተደረገ ባለመሆኑ የምእመናን ስጋት አሁንም እንደቀጠለ ነው ብለዋል፡፡

Mahibere kidusan tv
እቅበተ ተዋሕዶ
Photo
✍️የቤተ ክህነቱን የስፍና ዕዳ፣ ጭምር የተሸከመው ማኅበር✍️
+++
በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ የጥቂት ግለሰቦችን ፍላጎት መሠረት አድርገው የተሰባሰቡ እልፍ አእላፍ ስብስቦች (ማኅበራት) አሉ። ከጥቂቶች በቀር አብዛኛዎቹ ግብና ሥልታዊ ትኩረት የሌላቸው በሥጋዊ መሻት ብቻ የሚናውዙ ናቸው። ቤተ ክህነቱም ለአገልግሎት ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንን ለማቆርቆዝ የተመሠረተ #ጋግሪን ተቋም ከሆነ 50 ዓመታት ተቆጥረዋል። (ቤተ ክህነትና ቤተ ክርስቲያን ልዩነታቸውን ልብ ይሏል) ። ባለፈው የቤተ ክህነት ልኬተ ዘመነ ውስጥ ግን እነ ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስን የመሰሉ የንሥር ዓይን የተላበሱ አባቶችም አልፈውበት ነበር፣የዛሬውን አያድርገውና።

በ1980 ዎቹ እንደ ጠዋት ፀሐይ ቦግ ብለው ያጣናቸው አቡነ ጎርጎዮስ ካልዕን ስናስብ ልባችን ይደማል። ይሁን እንጂ እንደ ልቦናቸው መሻት እሳቸው ባሰቡት ልክና መጠን ባይደርስም ዛሬ ላይ ከፈጣሪ ቀጥለን የምንመካበት #ማኅበረ ቅዱሳን የሚባልን የአገልግሎት ተቋም በወኔ ለኩሰውልን አልፈዋል። በብጹዕነታቸው ዘመን የነበሩ እንደሚናገሩት አማናዊውን አገልግሎት "እኔ ለኩሸዋለው እናንተ አንድዱት" ይሉ ነበር ይባላል፣ አቡነ ጎርጎርዮስ ።

በአጭሩ በዚህ ዘመን ማኅበረ ቅዱሳን ማለት ቤተ ክህነቱ ሊሠራው የነበረውን አልፎም ራሱ ቤተ ክህነቱ የፈጠረውን እልቆቢስ ችግር ለመፍታት #መከራውን የሚያይ ማኅበር ነው። ማኅበሩን ቤተ ክህነቱ እንኳንስ ሊያግዘው፣ በታላቅ ትግስት ሁሉን ችሎ፣ የቤተ ክህነቱን ስንፍና ጭምር ተሸክሞ ቤተ ክርስቲያኒቱን በዓለም አደባባይ ከሐፍረት ሰውሮ ከአቅሙ በላይ እየደከመ በመላው ዓለም አገልግሎት እየሰጠ ያለ ብቸኛ ተቋም ነው።

በስብከተ ወንጌል፣ በማኅበራዊ አገልግሎት፣ በዕቅበተ እምነት፣ በገዳማት አገልግሎት በጥናትና ምርምር እና በሌሎችም ዘርፎች ያለውን ስር የሰደደ ክፍተት ለመሙላት ባለፉት 32 ዓመታት ዕረፍት አልባ ትግል እያደረገ እዚህ ደርሷል።

ቤተ ክህነቱ ግን በማይድን ዘውገኝነትና በሙስና እጅ ከወርች ታስሮ ይማቅቃል። የምእመናን የሐዘንና የመከራ ምንጭም ሆኖ ቀጥሏል፣ ቤተ ክህነቱ። ማኅበረ ቅዱሳን ግን ዛሬም ለአንዲት ቤተ ክርስቲያን ከአቅሙ በላይ እየሰራ ቀጥሏል። ምእመናን ከመቼው ጊዜ በላይ ማኅበሩን በቻልነው አቅም ሁሉ ልናግዝ ይገባል። የዓይናችን ማረፊያ ብቸኛ ተቋም ነውና።
ወደ ላይ አያዳልጣችሁ!
+++
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን አንድ ጨዋነት የራቀው ሰው ሰደባቸው አሉ። በኋላ ግን ጸጽቶት እግራቸው ላይ ወድቆ “ይማሩኝ፣ አጥፍቻለሁ፣ አድጦኝ ነው” ሲላቸው፣ እርሳቸውም “ታዲያ ወደ ታች ያድጣል እንጂ ወደ ላይ ያድጣል እንዴ?” አሉት ይባላል።

ወደ ላይ የሚያድጣቸውን ብዙ ሰዎች እያየን ነው። ሰሞኑን ዘነበ ወላ የተባለ ግለሰብ፣ ሊነቅፈው ቀርቶ ሊረዳውና ሊያደንቀው እንኳ እጅግ የሚበዛበትን የምናኔ ሕይወት ለመንቀፍ ሲሞክር ሰምተናል (የተነገረው በሕንድኛ ወይም በታይ ቋንቋ አይደለም!)። ይህን የመሰሉ እናውቃለን ከሚሉ አላዋቂዎች ወይም ጭፍን ጥላቻ ካሳወራቸው ሰዎች በኦርቶዶክሳዊነት ላይ በተለያየ መንገድ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች እየበዙ መምጣታቸው ጉዳዩን እንደ ቀላል ለማለፍ የማይቻል ያደርገዋል። ዛሬ ካለው የተከማቸ ኦርቶዶክስ-ጠልነት ያደረሱን ከ20ኛው መ/ዓ መጀመሪያ ጀምሮ ኦርቶዶክስ ጠል በነበሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ይሰነዘሩ የነበሩ የጥላቻ ንግግሮችና ጽሑፎች መሆናቸውን ልብ ይሏል።

ምናኔያዊ ሕይወት፣ ከትንሣኤ በኋላ የምናገኘውን እንደ መላእክት የመሆንን ሕይወት፣ በዚህ ዐለም ገንዘብ የማድረግ ሕይወት ነው። “በትንሣኤስ እንደ እግዚአብሔር መላእክት በሰማይ ይሆናሉ እንጂ አያገቡም አይጋቡምም” እንዳለ ጌታችን። ማቴ. 22፡30 መላእክት በተፈጥሯቸው እንደማያገቡና እንደማይጋቡ ሁሉ፣ ከትንሣኤ በኋላ ደግሞ ለሰዎችም ማግባትና መጋባት እንደማይኖር ሁሉ፣ መላእክት ዛሬ የሚኖሩትን፣ የሰው ልጆች ደግሞ ከሞት በኋላ የሚያገኙትን ሕይወት መናንያን ገዳማውያን በአሁኑ ሕይወት ይኖሩታል። እንደዚሁም ምናኔያዊ ሕይወት አዳም ከመበደሉ በፊት የነበረው ሕይወት ምን ይመስል እንደ ነበረ በመስታወት የሚያሳይ ነው፣ ጌታችን የሰጠውን ሕይወት በምልዓት የሚያሳይ ነው።

ምናኔያዊ ሕይወት በክርስትና ውስጥ ያለውን እጅግ የገዘፈና ዘርፈ-ብዙ የሆነ ነገረ-ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ ፋይዳ ለጊዜው ብናቆየው እንኳ፣ ክርስቲያናዊ ገዳማት ለሰው ልጆች ያበረከቷቸው ኢኮኖሚያዊ፣ እውቀታዊና ታሪካዊ ጠቀሜታዎች እጅግ በጣም ብዙ ናቸው። ጥቂቶቹን እንኳ ብናስታውስ፤ ዩኒቨርሲቲዎችና አዳሪ ት/ቤቶች በዋናነት የተቀዱት ከገዳማት ነው። የከፍተኛ ተቋማት ተማሪዎች ሲመረቁ የሚለብሱት ጋዋንና የሚደፉት ቆብ የገዳማትን ቀሚስና ሞጣህት እንዲሁም ቆብ የሚመስለው በአጋጣሚ አይደለም።

በአውሮፓ የውኃ ኃይልን ለወፍጮና ለቆዳ ሥራ መጠቀምንና ማዕድናትን ማውጣትንና መጠቀምን በስፋት ያስተዋወቁት ገዳማውያን ናቸው። የአውሮፓን የእርሻ መሬት፣ ሥነ ጥበብና እውቀት ከጥፋት በመጠበቅና በማበልጸግ ረገድ ገዳማት የተጫወቱት ሚና ምትክ አልባ ነው። አንዳንድ ገዳማት በየዓመቱ የአበምኔቶች መደበኛ ስብሰባ ስለነበራቸው፣ የደረሱባቸውን አዳዲስ የቴክኖሎጂ እውቀቶችና ልምዶች ይለዋወጡ ስለነበር በዚህ መንገድ ሥልጣኔ በመላው አውሮፓ እንዲስፋፋ የራሳቸውን ታላቅ ሚና ተጫውተዋል።

ከክርስትና በፊት የጉልበት ሥራ መልካም ክብርና ስም አልነበረውም። በግሪኮች ትምህርት መሠረት የጉልበት ሥራ የዝቅተኞቹ ኅብረተሰብ ክፍል (የድሀውና የባሪያዎች) ሥራ ተደርጎ ይወሰድ ነበር። በሮማውያን ዘንድም ለሥራ የነበረው መንፈስ ተመሳሳይ ነበር። ለጉልበት ሥራ በተለይም ለግብርና ከፍ ያለ ቦታና ከበሬታ የሰጡት ገዳማት ናቸው።

ከዚህም ጋር ገዳማት ለድሆች፣ ለስደተኞች፣ ለወላጅ አልባ ልጆች፣ ለሕሙማንና ለችግረኞች መጠጊያዎች በመሆን አገለግልዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በ4ኛው መ/ዓ የነበረው ቅዱስ ባስልዮስ የመሠረታቸው ገዳማት ሐኪም ቤቶች፣ የድሆች መመገቢያዎችና የችግረኞች መርጃ ማዕከሎችም ነበሩ። የዘመናዊ ሆስፒታል ጽንሰ-ሐሳብ መሠረቱ ክርስቲያናዊ ገዳማት ናቸው።

እንደዚሁም ገዳማት የሥነ ጽሑፍና የትምህርት ማዕከላት ነበሩ። ታላላቅ ቤተ መጻሕፍት የነበራቸው ብዙ ገዳማት ነበሩ። ብዙ መጻሕፍት ከእኛ እንዲደርሱ ያደረጉት መጻሕፍትን የሚሰበስቡና ባለሙያዎችን መድበው በእጅ የሚያስገለብጡ ገዳማት ናቸው። ብዙዎቹ መጻሕፍትና የታሪክ መዛግብት ከጥፋት ተርፈው ከዛሬ የደረሱት በገዳማት ተደብቀውና ተጠብቀው ስለኖሩ ነው።

ግሪኮች በኦቶማን ቱርክ በተገዙባቸው ወደ 300 የሚደርሱ ዘመናት ውስጥ እምነታቸውን ብቻ ሳይሆን ቋንቋቸውን፣ ባህላቸውንና ሥነ ጽሑፋቸውን ሕያው አድርገው የጠበቁት በገዳማት ዋና ማዕከልነት ነበር። ገዳማቱ ለካህናት ብቻ ሳይሆን በቱርኮች ግዛት ሥር ለነበሩ መላው ግሪካውያን ስውር ት/ቤቶች ነበሩ። በአገራችንና በሌሎች አገራትም ብዙ ተመሳሳይ ታሪኮች አሉ። ነጻነትን ለሚወዱና ባርነትን ለሚጸየፉ ሰዎች ሁሉ እነዚህ ትርጉማቸው ጥልቅ ነው። የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ገዳማትን ትቁር ጥምድ የሚያደርጓቸውም ለዚህ ነው።

መናንያን አባቶችና እናቶች ለሰው ልጅ ሁሉ ምሕረትን ከእግዚአብሔር የሚለምኑ ናቸው። በአስቄጥስ ገዳም ስለ ነበረ አባ ኢሳይያስ ስለ ተባለ አባት በመጽሐፈ ገነት እንዲህ ተብሎ እናገኛለን፡- “በዋዕየ ፀሐይ ላይ ራቁቱን ቁሞ ስለ መላው ዐለም ሲጸልይ ሳለ ከመነኰሳት አንዱ እንዲህ የሚል ድምጽ ሰማ፡- ‘ከእርሱ ጸሎት የተነሣ ለዐለሙ ሁሉ ምሕረት አድርጌያለሁና ሂድና ለአባ ኢሳይያስ ሰውነቱን የሚሸፍንበት ልብስ ስጠው።’”

ገዳማውያን መናንያን ሌላውን የሚዘርፉና የሚያጠፉ ሳይሆኑ ለሰው ልጆች ሁሉ ምሕረትን የሚለምኑ ናቸው፣ ሰውን የሚያሳድዱ ሳይሆኑ የተሰደዱትን የሚቀበሉ ናቸው። እንኳንስ የሰው ልጅ እንስሳትና አራዊት እንኳ አዳኞች ሲያሳድዷቸው ሸሽተው የሚጠጉባቸው ናቸው። የፍርሃትና የአጎብዳጅነት መንፈስ ያይደለ የእውነትና የጥብዓት መንፈስ ያለው ሁሉ ይህን ይረዳል።

ምንም እንኳ ምናኔያዊ ሕይወት ዓላማው በዚህ ዐለም ሀብት መበልጸግ ባይሆንም፣ በኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ረገድም ቢሆን ገዳማት በየዘመናቱ የነበራቸው ሚና ቀላል አልነበረም። ለአብነት ያህል በዘመናችን የግብፅን የእንስሳት ተዋጽዖ ምርቶች በከፍተኛ ድርሻ የሚሸፍኑት ኦርቶዶክሳውያን ገዳማት ናቸው። የአስቄጥስ ገዳም ለግብፅ የአየርና የዐፈር ጠባይ ተስማሚ የእህልና የአትክልት ዝርያዎችን በማምረት የአገሪቱን የምግብ አቅርቦት ችግር በመፍታት ረገድ የተጫወተው ሚና ታላቅ ነው።

በተለይም ደግሞ የአስቄጥስ ገዳም መነኰሳት በሳይንሳዊ ምርምር በግብፅ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ ያመረቱት “ፎደር ቢት” (fodder beet) የተሰኘ የስኳር ድንች ዓይነት አዲስ ምርት በእጅጉ ተመስግነውበታል። የአሰቄጥስ ገዳም መነኰሳት በዚህ ረገድ ላበረከቱት አስተዋጽዖ ሙስሊሙ መሪ አንዋር ሳዳት ከታላቅ ምስጋና ጋር ብዙ ሽልማት አበርክቶላቸዋል። ሌሎቹ የግብፅ ገዳማትም ለበረሃው ተስማሚ የሆኑ የዕፅዋትና አዝዕርት ዓይነቶችን በሳይንሳዊ ምርምር በመፈለግ ረገድ ከፍተኛ ሥራ እየሠሩ ናቸው።

ወደ ግብጽ አባ ቢሾይ ገዳም ተጉዞ የነበረ አህመድ ኤል-ጋማል የተባለ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬትስ ጋዜጠኛ November 21, 1988 ላይ በወጣ “Khaleeg” በተባለ ጋዜጣ ላይ “A visit to the Depth of the Desert” በሚል ርዕስ እንዲህ ጽፎ ነበር፡-
“በአባ ቢሾይ ገዳም ከአባቶች መነኰሳት ጋር ተገናኘሁ። በዚያም የቦታውን መንፈሳዊነትም ሆነ የእንግዳ ተቀባይነታቸውን ነገር፣ እንዲሁም ዘርፈ ብዙ የሆነውን ተግባራቸውንና ትምህርታቸውን ተመለከትሁ፤ ሆኖም ግን ካየሁት ሁሉ አንዱንም እንኳ እንደሚገባ አድርጌ አሟልቼ ልገልጸው አልችልም። ሆኖም የክርስትና ገዳማዊ ሕይወት በታሪካችን ውስጥ የነበረውን ሚና መዘንጋት ለእያንዳንዱ ዐረብ ታላቅ ኪሳራ የመሆኑ ነገር ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ማስተዋል ተገቢ መሆኑን ለራሴ ተረድቻለሁ። በእ*ስልምና ሃይማኖት ውስጥ ምንኲስናና ገዳማዊ ሕይወት የሚባል ነገር አለመኖሩን ማሰብ ውስጥን የሚረብሽና የሚያሳዝን ነገር ነው።”

መናንያን በሥራ የሻከሩ እጆች ያሏቸው ብቻ ሳይሆኑ ከርኩሰትና ከነውር ንጹሕ የሆነች ነፍስ ትኖራቸው ዘንድ የሚጋደሉ እውነተኛ ጀግናዎችና ትክክለኛ ፈላስፋዎች ናቸው። ከመብላትና መጠጣት፣ ከማግባትና ከመጋባት ባሻገር ወዳለው ሰማያዊ ሕይወት የሚያመለክቱ አቅጣጫ ጠቋሚዎችና ዐዋጅ ነጋሪዎች ናቸው።

ስለሆነም ሰው ያልደረሰበትን ነገር በመሰላል ወጥቼ ልንቀፍ ማለት ተገቢ አይደለም! ሊታገሡት የሚገባም አይደለም! በዕድሜያቸውም ሆነ በእውቀታቸው ታዳጊ የነበሩት የ1950ዎቹና 60ዎቹ ትውልዶች በኦርቶዶክስ-ጠል መምህራን የተሞሉት ጥላቻ ዛሬ ያፈራውን መራራ ፍሬ እያየን፣ የእነዚያ የመንፈስ ልጆች የሆኑ በዕድሜ እንኳ ባይሆን በአእምሮ ሕፃናት የሆኑ ኦርቶዶክስ-ጠሎች ተገቢ ያልሆኑ ነገሮችን ሲናገሩና ሲጽፉ እያዩ ኦርቶዶክሳውያን ዝም ማለት አይችሉም።

ኦርቶዶክሳውያን፣ ገና ለገና ያሻንን ብንላቸው ለክፉ አይሰጡንም የሚሉ የፈሪዎችና የአጎብዳጆች የብዕር መፈተኛና የአፍ ማሟሻ መሆንን መቀበል ከማይችሉበት የመጨረሻ ደረጃ ላይ ደርሰዋል። ስለዚህ ወደ ላይ አያዳልጣችሁ! የሚታየውን ብቻ ሳይሆን የማይታየውን መፍራትም ብልህነት ነው!
(መ/ር ዶክተር ያረጋል አበጋዝ)
✝️እውቀት #ከማጣት የተነሣ እየጠፋ ያለው ሕዝብ✝️
+++
ወጣቱን በአግባቡ አለማስተማራችን ገና ዋጋ ያስከፍለናል። ቤተ ክርስቲያን እንደማንኛውም ምድራዊ ተቋም ሁሉን ነገር የምትቀበል ትመስለዋለች። ወጣቱ በጸጋው ግምጃ ቤት ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንና በሰፈሩ በተደረደሩ ተራ የድንጋይ ካብ የሆኑ ሕንጻዎች መካከል ያለው ድንበር ጠፍቶበታል።

በደስ ይላልና ምን ችግር አለው በሚሉ የድንቁርና ማደንዘዣ ታጅበው እየተፈጸሙ ያሉ ልምምዶች እየተለመዱ መጠዋል። እጅግ ከባድ ፈተና መሆናቸው አይቀርም። ወጣቶች እባካችሁ ልብ ግዙ። ለብልጭልጭ #አሸንክታብ የምትሯሯጡትን ጊዜ ቀንሱና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንና ትምህርተ አበውን ለመማር ለማንበብ ፣ለመጠየቅ ጥቂት ጊዜ ስጡ። ያኔ ዛሬ እያደረጋችሁት ባለው ታፍራላችሁ።
በዚህ #የትምህርት ቁሳቁስ የድጋፍ ማሰባሰብ ዘመቻ በመሳተፍ የነገ ሀገር ተረካቢዎችን ተስፋ እናለመልም ዘንድ ማኅበረ ቅዱሳን ጥሪ አቅርቧል።
እንረባረብባት።
ዝክረ ሰማዕታተ #ሻሸመኔ 2ኛ ዓመት::

ቅድስት በረከታቸው ይደርብን አሜን!!!
https://yangx.top/Apologey